የ10ኛና የ12ኛ ክፍል የሀገር አቀፍ ፈተና ከግንቦት 26 እስከ ሰኔ 4 እንደሚሰጥ ተገለጸ

አዲሰ አበባ ሚያዚያ30/2000/ዋኢማ/በዘንድሮው የትምህርት ዓመት የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከግንቦት 26 እስከ ሰኔ አራት እንደሚሰጥ የአጠቃላይ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫና የፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።ለፈተናው የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች መጠናቀቃቸው ተገልጿል።

የኤጀንሲው ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ አቶ ታከለ ገብረ ኪዳን ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ ኤጀንሲው በዘንድሮው የትምህርት ዓመት ለ10ኛና ለ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የሀገር አቀፍ ፈተናን በ768 ጣቢያዎችና በ1ሺ 236 አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች ለመስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቋል።

ፈተናው ለ10ኛ ክፍል ተፈታኞች ከግንቦት 26 እስከ ግንቦት 29 ፤ለ12ኛ ክፍል ደግሞ ከሰኔ 2 እስከ ሰኔ 4/2000/ዓ.ም እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በዘንድሮው የትምህርት ዓመት ከአስረኛ ክፍል ተፈታኞች መካከል 522 ሺ 783 በመደበኛ፣ 425ሺ 717 በግል እንዲሁም 13ሺ 141 ያህሉ በማታው ክፍለ ጊዜ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፤ ከ12ኛ ክፍል ደግሞ 91ሺ 637 በመደበኛ፣ 23 በማታ መርሀ ግብር መሆኑን ገልጸዋል።

የ10ኛ ክፍል የተፈታኞች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ206ሺ 777 ፣ የ12ኛ ክፍል ደግሞ በ20ሺ 462 ተፈታኞች ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

የፈተናውን ህትመት በየጣቢያዎቹ ለማጓጓዝ በአሁኑ ወቅት ዝግጅቱ መጠናቀቁንና በተፈታኞች የፈተና አዳራሽ መግቢያ ካርድ ላይ የስም፣የምዝገባ ቁጥር፣ የጣቢያ ኮድ ስተቶች ባሉባቸው ካርዶች ላይ ደግሞ የማስተካከያ ስራ እየተሰራ መሆኑንና በየጣቢያው የተመደቡ ሱፐርቫይዘሮች ወደየአካባቢው ይዘው እንደሚሄዱ ጠቁመዋል።

ፈታኞችና ሱፐርቫይዘሮች በሚሰሩባቸው ትምህርት ቤቶች የማይፈትኑ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ጠቁመው፤ በፈተናው ወቅት ለመቀዳዳት፣ በቡድን ለመስራት፣ አሰገድዶ የፈተና መልስ ለመንጠቅ በሚሞክሩ ተፈታኞች ላይ እረምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል።

እንዲሁም ተፈታኞች ለኦሬንቴሽን በሚጠሩበት ቀንና በፈተናው ዕለት የራሳቸውን መታወቂያና የፈተና አዳራሽ መግቢያ ካርድ በመያዝ ስዓት አክበረው መገኘት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ፈተናውን መስራት ከመጀመራቸው በፊት ወደ ፈተና አዳራሽ መግቢያ ካርዳቸው ላይ ያሉትን መረጃዎች በጥንቃቄ መሙላት እንሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በፈተናው ጣቢያዎችና አዳራሾች ሞባይልና የሂሳብ ማሽን ይዞ መግባት በፍጹም የተከለከለ መሆኑን ተፈታኞች ከወዲሁ ማወቅ እንዳለባቸው አቶ ታከለ አስረድተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው ፈተና የተሳካ እንዲሆን የክልል፤ የዞንና የወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች በባለቤትነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አቶ ታከለ ጥሪ ማቅረባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።