አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2000/ዋኢማ/ ኢትዮጵያ ለሴቶች እኩልነትና ተጠቃሚነት ትኩረት በማድረግ ውጤታማ ስራ በመስራት ላይ እንደምትገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በዕርዳታ የሚገኘው ገንዘብ የሴቶችን እኩልነትና ተጠቃሚነት በማስመልከት በሒልተን ሆቴል ዛሬ በተካሄደ ጥናት ላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ልማት ፈንድ ሀላፊ ሚስስ ሌቲ ቺዋራ በተለይ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ የፆታን እኩልነት ያረጋገጡ በርካታ የልማት ስራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው።
በአገሪቱ ሴቶች ተሳትፊነታቸውን የሚያረጋግጡ ፖሊስዎችንና ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኙም ሃላፊዋ ጨምረው ገልጸዋል።
በሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ፖሊስና ስትራቴጂ አፈፃፀም መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ኢትዮጵያ የስነ ፆታን እኩልነት ያረጋገጠ ስርዓት በመመስረት በብድርና ዕርዳታ ወደ አገር ውስጥ የሚገባን ገንዘብ ሴቶች እንዲጠቀሙ በማድረግ ላይ መሆኗን ጠቁመው፤ በዚህም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የተሻለ ውጤት ማስመዝገቧን አስረድተዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፈንድ የኢትዮጵያ ተወካይና የጥናት አስተባባሪ ወይዘሮ አፀደ ዘርፉ በበኩላቸው፤ ጥናቱ በዕርዳታ አሰጣጥ ላይ የፓሪስን ስምምነት መሰረት ባደረገ መልኩ ላለፉት አምስት ወራት መካሄዱን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የዕርዳታ ገንዘብ ሴቶችን ምን ያህል ተጠቃሚ እንዳደረገ ለመገንዘብ የተካሄደው ጥናት መሰረት ያደረገው ከሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች መሆኑን የጥናቱ አዘጋጆች አስታውቀዋል።
ጥናቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ልማት ፈንድ የገንዘብ ድጋፍና በኢትዮጵያ ሴቶች ጉዳይ ማህበር የተካሄደ ሲሆን፤በውይይቱ ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተወጣጡ 50 ያህል ተወካዮች መሳተፋቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።