አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2000/ዋኢማ/ በደቡብ ኦሞ ዞን ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራታቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ። በዞኑ የመጀመሪያው የኢንቨስትመንት ፎረም ትናንት ተካሂዷል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በኢንቨስትመንት ፎረሙ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳስታወቁት፤ ባለሃብቶቹ የተሰማሩት በእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት፣ በግብርና፣ በእጣንና ሙጫ እንዲሁም በሆቴሎችና ማዕድን ልማት መስኮች ነው።
ዞኑ ለኢንቨስትመንት የሚሆኑ የተለያዩ አማራጮች እንዳሉትና ለባለሃብቶች ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደረግ በተግባር መታየቱን ጠቁመው፤ ሌሎችም ባለሃብቶች ወደ ዞኑ በመምጣት በፈለጉት የስራ መስክ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፉት ስርዓቶች የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ የዞኑ ነዋሪዎች ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋልጠው መቆየታቸውን ጠቁመው፤ አሁን ተግባራዊ በመደረግ ላይ በሚገኘው የገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት ተሳትፎ ከሚያደርጉ ባለሃብቶች ልማት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በፎረሙ ላይ በዞኑ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጡ ባለሃብቶች ሽልማት እንደተሰጠ የዞኑን ማስታወቂያና ባህል ማስተባበሪያ ዋና መምሪያን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።