ተማሪዎች በየትምህርት ቤቶቻቸው ጤናቸው ተጠብቆ እንዲማሩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተገለጸ

አዳማ ሚያዚያ 30/2000/ዋኢማ/ ተማሪዎች በየትምህርት ቤቶቻቸው ጤናቸው ተጠብቆ እንዲማሩና ብቁ አገር ተረካቢ ዜጎች እንዲሆኑ ለማስቻል ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። በትምህርት ቤቶች የሚታዩትን የሳኒቴሽን፣የውሀና የሀይጂን ችግር ለመቅረፍ በተዘጋጀው አዲስ የተግበር መመሪያ ላይ በአዳማ ከተማ ውይይት እየተደረገ ነው።

በሚኒስቴሩ የኢንዱስትሪና የተቋማት ሀይጂን ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ሲለሺ ታዬ በሀገር አቀፍ አውደ ጥናቱ ላይ እንደተናገሩት ተማሪዎች ያለሙትን የትምህርት ራዕይ ግቡ እንዲያደርሱና ብቁ ዜጎች በመሆን የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን እንዲያደርጉ በየትምህርት ቤቶች ጤናቸው ተጠብቆ ሊማሩ ይገባል።

የትምህርት ሚኒስተርናየውሀ ሀብት ሚኒስቴር ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር በመላ አገሪቱ በተመረጡ በ2ሺ13 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያደረጉት የናሙና ጥናት እንደሚያመለክተው መጽዳጃ ቤት ያላቸው 76 በመቶ የሚሆኑት ብቻ መሆኑንና ይህም በአማካይ በአንድ ጉድጓድ ከ171 በላይ ተማሪዎች እንደሚጠቀሙ ያሳያል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ተማሪዎች የንጹሕ መጠጥ ውሀና የእጅ መታጠቢያ እንደሌላቸው ገልጸው ባጠቃለይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአሁኑ ጊዜ 15 ሚሊየን ያህል ተማሪዎች ይማሩበታል ተብሎ ከሚገመቱት 21ሺ ያህል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል አብዛኛዎቹ የንጹህ ውሃ እጥረትና የሀይጂን ችግር እንዳለባቸው አመልከተዋል።

በአከባቢያችን 60 በመቶ የሚሆኑት ተላላፊ በሽታዎች በአካባቢ ንጽህና ጉድለት የሚመጡና 250 የሚሆኑት ሰዎች ሕይወታቸው በዚሁ ምክንያት በየዓመቱ እንደሚያልፍ የተናገሩት ቡድን መሪው ተማሪዎችም የአከባቢያቸውና የትምህርት ቤታቸው ንጽህና ካልተጠበቀ በተላላፊ በሽታዎች ሕይወታቸው ሊቀጠፍ የሚችል በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በትምህርት ቤቶች የሚከሰቱትን የሳኒቴሽን፣ የውሀና የሀይጂን ችግሮችን ለመቅረፍ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከትምህርትና ውሀ ሀብት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይሄው የተግበር መመሪያ ባለሙያዎቹ ተገቢውን ውይይት አድርገው አስተያየታቸውን ከሰጡ በኋላ በሚቀጥለው ዓመት በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንደሚሆን አስታወቀዋል።

መመሪያውንም በገጠር የተሰማሩ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ከመምህራን፣ ከተማሪዎችና ከአከባቢው ሕብረተሰብ ጋር በመተባበር ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ገልጸው ሦስቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ደግሞ በጋራ በመተባበር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አመልከተዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ከ11 ክልሎች የተውጣጡ የትምህርት፣የጤና ባለሙያዎችና ከሦስቱም የትምህርት፣የጤናና ውሀ ሀብት ሚኒስቴሮች የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።