እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እርዳታ ሰጠች

አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2000/ዋኢማ/ ኢትዮጵያ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት የምታደርገውን ጥረት የሚረዳ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እርዳታ የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ መስጠቱን አስታወቀ።

ትናንት በኤምባሲው ፅህፈት ቤት የዓለም አቀፍ መምሪያ ኃላፊ ሚስተር ፖል አክሮይድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ አገሪቱ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት የሚረዳትና ለቀጣዩ አንድ ዓመት የሚያገለግል 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ተስጥቷታል።

የገንዘብ እርዳታው በዋናነት የሚውለው በአገሪቱ ለሚከናወኑ የድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞች መሆኑን ጠቅሰው፤ ከነዚህ መካከል ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት እንዲሁም ውሃና ሳኒቴሽን ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2000 ጀምሮ እድገት እያስመዘገበች መሆኑን ኃላፊው ገልፀው፤ የኢኮኖሚ ዕድገቱም ላለፉት 4 ዓመታት ከ10 በመቶ በላይ ማስመዝገብ መቻሏንና ባለፉት 10 ዓመታት የድህነት መጠኑ ከ46 ወደ 36 በመቶ መቀነሱንም አስታውሰዋል።

በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ለውጥ እያየን ነው ያሉት ኃላፊው በትምህርት፣ በውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም በጤናው ዘርፍ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት ተጨማሪ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋት ገልፀው፤ የእንግሊዝ መንግስት ዛሬ የሰጠው 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብርም መንግስታችን አገሪቱ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል።

ላለፉት 4 ዓመታት የዓለም አቀፍ ልማት መምሪያ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ እንዲጠናከር፣ የትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት እንዲስፋፋ ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ዋናው ትኩረታቸው መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማዳረስ እንደነበር አስረድተዋል።

በተለይ ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት መንግስታቸው 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልፀው፤ በገንዘቡ 6 ነጥብ 5 ሚሊየን የአልጋ አጎበሮችን፣ የወባ መድሃኒትና የወሊድ መከላከያ ገዝቶ ማከፋፈሉንና የትምህርትና የጤና ሙያተኞችን የተለያዩ ክፍያዎች ለመሸፈን ማስቻሉን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ኖርማን ሊንግ በበኩላቸው የእንግሊዝ መንግስት ኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ገልፀው፤ ዘንድሮ የተሰጠው ድጋፍ በእጥፍ ማደጉ ይህን ያመላክታል ብለዋል።

ለኢትዮጵያ የምናደርገው ድጋፍ ከስድስት ዓመት በፊት 180 ሚሊየን ብር እንደነበረ አምባሳደሩ አስታውሰው ድጋፉ ዘንድሮ ወደ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን አድጓል ብለዋል፡፡

እንግሊዝ ለአፍሪካ አገራት ከምትስጠው ድጋፍ ኢትዮጵያ ትልቁን ድርሻ እንደምትወስድ መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።