መቀሌ ሚያዝያ 30/2000/ዋኢማ/ የዓዲግራት ከተማ ወጣቶች በፀረ-ድህነቱ ትግል ተሳትፈው ራሳቸውን በመለወጥ የልማት ሞዴል ለመሆን እንደሚጥሩ በውሳኔያቸው አረጋገጡ ፡፡
በከተማው የሚገኙ ከ500 በላይ ወጣቶች፣ የአመራር አካላትና ወላጆች የተሳተፉበትና ለአንድ ቀን ያካሄዱትን ኮንፈረንስ ሲያጠናቅቁ ባስተላለፉት ውሳኔ በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዳስትሪ በመሰማራት ራሳቸውን ለመለወጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል ።
የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች እንደገለጹት በአንዳንድ ወጣቶች ዘንድ የልማት ፓኬጁን በተገቢ መንገድ ተገንዝቦና ተቀብሎ ወደ ተግባር ያለመግባት፣ ሥራ የማማረጥና የመናቅ ሁኔታ የሚታይ ቢሆንም በርካታ የከተማው ወጣቶች ወደ ሥራው ገብተው ኑሮአቸቸውን ሲለውጡ በማያታቸው የነሱን ፈለግ እንደሚከተሉ አረጋግጠዋል ።
የኮንፈረንስ ተሳታፊዎቹ የሚመለከታቸው አካላት ለወጣት ተኮር ፓኬጅ ተገቢ የሆነ ብድር በወቅቱ ያለመስጠትና ተደራጅተው ሥራ ለጀመሩ ወጣቶችም ሙያዊ ድጋፍ የመስጠት እጥረት እንዳለ አመልክተዋል ።
በተለይም እጥረቱ የሚታየው በከተማው ንግድ፣ ኢንዳስትሪና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤትና በከተማው ማዘጋጃ ቤት ሲሆን የወጣቶችን ችግር ፈጥኖ በመፍታቱ ረገድ ተግባብቶ ያለመሥራት ጉድለትም እንደሚታይ ጠቁመዋል ።
በኮንፈረነሱ ላይ የተገኙት የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ብርሃነ ጸጋይ ወጣቶቹ ያነሱት ችግሩ መኖሩን አምነው ካሁን በኋላ ግን መስተዳደሩ ከሚመለከታቸው ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመወያየት እንደሚፈቱላቸው አረጋግጠዋል፡፡
ወጣቶች በአገር ግንባታና በፀረ-ድህነት ትግል የጎላ ድርሻ እንዳላቸው የተናገሩት ምክትል ከንቲባው ወጣቶቹን በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ለማሰማራት የሚያስችል ግንዛቤን በማስፋት ረገድ የተጠናከረ ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ገልጸዋል።
የከተማው ወጣቶች ጉዳይና ስፖርት ጽሕፈትቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ካሕሳይ በበኩላቸው በከተማው 1ሺ 200 ወጣቶች፣ወጣት ተኮር በሆነ ፓኬጅ በመታቀፍ ኑሮአቸውን ለመለወጥ እየጣሩ መሆናቸውን ጠቁመው በሥራ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን ለማቃለል ኮንፈረንሱ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል ።
በኮንፈረንሱ ላይ በሥራቸው የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ 40 ወጣቶች የምስክር ወረቀትና ከ30 ሺ እስከ 75 ሺ ብር ካፒታል ላስመዘገቡ አራት ወጣቶች ደግሞ የዋንጫ ሽልማት ከምክትል ከንቲባው እጅ መቀበላቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።