ኮሚሽኑ የቦንጋና የዲማ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች መዘጋታቸውን አስታወቀ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 29/2000/ዋኢማ/ በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙትን የቦንጋና ዲማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች በይፋ መዝጋቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን አስታወቀ። በጣቢያዎቹ ተጠልለው የነበሩ 23 ሺ የሱዳን ስደተኞች በኮሚሽኑ ድጋፍ ተጠቃለው ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ገልጿል።

ኮሚሽኑ በድረ ገጹ ይፋ ባደረገው ዘገባ እንዳስታወቀው፤ በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙት ሁለቱ የስደተኞች ጣቢያዎች እንዲዘጉ የተደረገው በጣቢያዎቹ ተጠልለው የነበሩ ስደተኞች በደቡባዊ ሱዳን ወደ ሚገኘውና መኖሪያቸው ወደ ነበረው ብሉናይል ክፍለ ሃገር ከተመለሱ በኋላ ነው።

ከሁለቱ ጣቢያዎች ስደተኞችን ወደ አገራቸው የመመለሱ ስራ ከተጀመረበት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከግንቦት 2006 ወዲህ 28 ሺ የሚደርሱ ሱዳናውያን ከጣቢያዎቹ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ኮሚሽኑ አመልክቶ ከነዚህ መካከል 2ሺ ያህሉ በራሳቸው መንገድ ወደ ትውልድ ስፍራቸው የተመለሱ መሆናቸውን ገልጿል።

አሁን በተዘጉ ሁለቱ ጣቢያዎች የቀሩ 3ሺ የሚጠጉ ስደተኞች ጋምቤላ ክልል ወደሚገኘው የፊኝዶ ጣቢያ ወይም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ወደሚገኘው የሸርቆሌ መጠሊያ ጣቢያ እንደሚተላለፉ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ መንግስትና ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ በሚገኘው ቡድኑ አማካኝነት የስደተኞች መጠለያ የነበሩት ካምፖችና መሰረተ ልማቶች ለአካባቢው ማህበረሰብ ግልጋሎት ሊሰጡ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እየሰራ መሆኑን አመልክቷል።

በጣቢያዎቹ ውስጥ የሚገኙ የውሃ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ ቢሮዎች፣ የሙያ ማሰልጠኛዎችና የመኖሪያ አካባቢዎችን ከነቁሳቁሳቸው ለነዋሪዎች የማስረከብ ስራ እንደሚሰራም ኮሚሽኑ ጠቁሟል።

የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ከ30 ሺ የሚበልጡ የሱዳን ስደተኞች በፈቃደኝነት ከኢትዮጵያ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መርዳቱን ድረ ገጹ አመልክቷል።

ከኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ መካከለኛው አፍሪካ፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክና ኬኒያ ወደ አገራቸው ከተመለሱት 275ሺ የሱዳን ስደተኞች መካከል 125ሺ ያህሉ በኮሚሽኑ ድጋፍ የተመለሱ መሆናቸውን ማመልከቱን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።