አዲስ አበባ ሚያዚያ 29/2000/ ከተለያዩ አገራት ቡናን በመግዛትና በማሰራጨት በሰሜን አሜሪካ በትልቅነቱ ሁለተኛ ደረጃ የያዘው ካሪቡ ቡና የቡና አምራቾችን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ የኢትዮጵያን ቡና ለማሰራጨት መስማማቱን አስታወቀ።
ሲ ኤስ አር ዋዬር የተባለ የዜና ድረ ገጽን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደዘገበው፤ ካሪቡ ቡና የኢትዮጵያ የቡና ምርቶች ለማሰራጨት የሚያስችለውን ፍቃድ አግኝቷል።
ካሪቡ ቡና ባገኘው ፍቃድ መሰረት የቡና አምራቾችን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ የኢትዮጵያን የቡና ምርቶች እንደሚያከፋፍል ዘገባው አመልክቷል።
ካሪቡ ቡና ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ከፈጸመ በኃላ የደርጅቱ የስራ ሀላፊ ሚስተር ፓወል ቱሬክ እንደተናገሩት ፤ ድርጅቱ ባገኘው ፍቃድ ለሸማቾች የኢትዮጵያን ቡና ጥራት በማስተዋወቅ የቡና አምራቾችን ሕይወት የመለወጥ ስራ ይሰራል።
የኢትዮጵያ አእምሮኣዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቱ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ የቡና አምራቾችን ጥቅም ማስጠበቅን ቅድሚያ በመስጠት በመስራት ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ስምምነቱ የዚሁ አካል መሆኑን መግለጻቸውን ሲ ኤስ አር ዋዬር የተባለ የዜና ድረ ገጽን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልዘግቧል።