አዲስ አበባ ሚያዚያ 29/2000/ዋኢማ/ ኤርትራ የጂቡቲን ድንበር ጥሳ በመግባቷ የተፈጠረውን የሁለቱ ሀገራት የድንበር ላይ ፍጥጫ ወደ ግጭት እንዳያመራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጣልቃ እንዲገባ ጂቡቲ ጠየቀች።
ኤ ኤፍ ፒን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደዘገበው፤ ኤርትራ የጂቡቲን ድንበር ጥሳ መግባቷን ጅቡቲ ማስታወቋን ገልጾ ፍጥጫው ወደ ጦርነት እንዳያመራ የፀጥታው ምክር ቤት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርባለች።
የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር መሐመድ አሊ ዩሱፍ ለዜና ምንጩ እንደተናገሩት፤ ኤርትራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ ጦሯን በማከማቸት ላይ ብትሆንም ሀገራቸው የጦርነት ውጥረቱን በአፍሪካ ህብረትና በአረብ ሊግ አማካይነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ቅድሚያ ሰጥታለች ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለወቅቱ የፀጥታው ምክር ቤት ሊቀመንበር ለሆኑትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእንግሊዝ አምባሳደር ጆን ሳዌርስ በፃፉት ደብዳቤ ፤ ኤርትራ ጦሯን ከጅቡቲ ድንበር እንድታስወጣ ያደረገችው ጥረት ውጤት አልባ መሆኑን አመልክተዋል።
በአሁኑ ጊዜ የሁለቱ አገራት ጦር ራስ ዱመራ በተባለ የድንበር ላይ ተራራ ተፋጠው የሚገኙ ሲሆን፤ ቦታው በቀይ ባህር የሚንቀሳቀሱትን መርከቦች በርቀት ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ሚስተር መሐመድ አሊ ዬሱፍ አስታውቀዋል።
ኤርትራ በማን አለብኘነት የጂቡቲን ድንበር ጥሳ የገባችው ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለውን የራስ ዱመራ አካባቢን ለመያዝ ካላት ፍላጎት መሆኑንና ኤርትራ የአገራቸውን አንድነትና ልአላዊነት መድፈሯን አመልክተዋል።
እንደዜና ምንጩ ዘገባ፤ የኤርትራ ጦር ወደ ጂቡቲ ድንበር በመዝለቅ በብዙ መቶ ሜትሮች የሚቆጠር ምሽግ በመቆፈር ላይ ነው።
ጂቡቲ የድንበር ፍጥጫውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ባቀረበችው ግብዣ መሰረት የአረብ ሊግ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ በማካሄድ የሊጉ ዋና ፀሐፍ ሚስተር አመር ሙሳ ጉዳዩን የሚያጣራ አንድ ቡድን ወደ አካባቢው እንዲልኩ ከውሳኔ ላይ መድረሱን ዘገባው አመልክቷል።
የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ የድንበር ውዝግቡን ሁለቱ አገራት በሰላማዊ ሁኔታ በውይይት እንዲፈቱ ባለፈው ሳምንት ጥሪ ማስተላለፉን ዘገባው አብራርቶ ኤርትራ በበኩሏ ጦሯ የጂቡቲን ድንበር ጥሶ እንዳልገባ አስተባብላለች።
ጂቡቲና ኤርትራ በድንበር ጉዳይ ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ መጋጨታቸውን ኤ ኤፍ ፒን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።