በኤርትራ ያለው አምባገነን ስርዓት ህዝቡ እምነቱን በነጻነት እንዳያራምድ የሚያደርገው ጫና መጠናከሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 28/2000/ዋኢማ/ የኢሳያስ መንግስት ኤርትራውያን በአገራቸው ዕምነታቸውን በነጻነት እንዳያራምዱ እንደሚከለክልና የሃይማኖት ነጻነትን እንደማያከብር ሁለት የሃይማኖት አባቶች አስታወቁ። ኤርትራውያን በተባበረ ትግል ጨቋኙን አገዛዝ እንዲያስወግዱም ጥሪ አቅርበዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ በኤርትራ የሁሉም ዕምነት ተከታዮች ዕምነታቸውን በነጻነት ማራመድ የሚችሉበት ሁኔታ የለም።

የኤርትራ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አባት የሆኑትና በለንደን በስደት ላይ የሚገኙት አባ ኃይለማሪያም ዘርዓዮሃንስ እንደገለጹት፤ የኢሳያስ አምባገነን አገዛዝ በአገሪቱ ሙስሊሞች ላይ በቀጥታ ከሃይማኖቱ ጋር የተያያዙ ድርጊቶችን ለምን ፈጸማችሁ በማለት የዕምነቱን መሪዎችና ተከታዮች በማሳደድና በማሰቃየት የጀመረውን ፀረ እምነት እንቅስቃሴ በሌሎች እምነቶችም ላይ ቀጥሎበታል።

ተሳታፊዎች

በኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማኞችም ላይ እያደረሰ ያለው በደል በእምነቱ የማይፈቀደውን ፓትርያርክን አውርዶ አዲስ እስከመሾም የሚደርስ መሆኑን ገልጸው በወንጌላውያንና በካቶሊክ ዕምነት ተከታዮችም ላይ በደል ማድረሱን እንደገፋበት አመልክተዋል።

ኤርትራውያን የሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮች አንዱ ሲነካ ሌሎቹ በጋራ ባለመቃወማቸው አምባገነኑ መንግስት ለሚከተለው ነጣጥሎ የማጥቃት ፖሊሲ መጋለጣቸውንና የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን አመልክተው፤ ህዝቡና የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይሎች በተባበረ ክንድ አምባገነኑን ስርዓት መጣልና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የኤርትራ ሙስሊም ማህበረሰብ የሃይማኖት መሪ የሆኑት መሃሙድ መሃመድ ኡስማን አልአሚን በበኩላቸው፤ መንግስቱ በሁሉም እምነቶች መሪዎችና ተከታዮች ላይ የሚያደርሰው በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

ህዝቡን በማሰር፣ በግዳጅ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በመላክና የዕምነት ቦታዎችን ባለማክበርና የሃይማኖት መሪዎችን በማሰር እምነትን በነጻ የማራመድ መብትን እንደሚጥስ ገልጸው፤ ህዝቡና የአምባገነኑ ስርዓት ተቃዋሚዎች በጋራ የሚያካሂዱትን ትግል ማፋፋምና ነጻነታቸውን ማስከበር ይገባቸዋል ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ጎረቤት አገሮችም በስርዓቱ በሚደርስባቸው ግፍና በደል ከአገራቸው ለሚሰደዱ ዜጎች እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ ስርዓቱን ለመጣል የሚደረገውን ትግል በማገዝ ለኤርትራውያን እፎይታ እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።