ሐረር መጋቢት 18 /2000/ዋኢማ/ በሐረሪ ህዝብ ክልል በዘንድሮው ግማሽ የበጀት ዓመት በማህበራዊና ምጣኔሃብታዊ ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ሙራድ አብዱል ሀዲ ዛሬ በተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት 3ኛ ዙር 3ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደገለጹት በክልሉ ባለፉት 6 ወራት በኢንቨስትመንት ፣በጤናና በትምህርትና በሌሎችም ዘርፎች የተከናወኑ የልማት ሥራዎች አበረታች ናቸው።
በዚህም መሠረት በተጠናቀቀው ግማሽ የበጀት ዓመት በክልሉ ከ72 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በመከናወን ላይ ካሉት የ20 ነባርና 10 አዳዲስ ፕሮጀክቶች መካከል አብዛኞቹ ለመጠናቀቅ ጥቂት ስራዎች ብቻ እንደቀራቸው አቶ ሙራድ ገልጸዋል።
በተለይ በዘንድሮ ዓመት ከተጀመሩት 10 ፕሮጀክቶች መካከል ከፍተኛውን የበጀት ድርሻ የያዘውና በአንድ የቻይና የመንገድ ስራ ድርጅት የሚሰራው የ14 ኪሎ ሜትር መንገድ ስራ የክልሉ ምክርቤት አፈጉባኤ ህንጻ ፕሮጀክትና የባህል ማዕከል ፕሮጀክት ይገኙበታል ብለዋል።
የክልሉን ገቢ ለማሳደግ በተደረገው ጥረትም ከቀጥታ ታክስ፣ቀጥታ ካልሆነ ታክስና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች ከ15 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቅሰው ይህም በእቅድ ከተያዘው ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።
የምዕተ ዓመቱን የትምህርት ግብ ለማሳካትም በክልሉ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ 10 ሺህ ህጻናት በሙሉ ትምህርት እንዲከታተሉ መደረጉን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
የክልሉን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ለ3ሺህ 438 ህጻናት የክትባት ፤ለ1ሺህ258 እርጉዝ ሴቶች የማዋለድ አገልግሎት የምግብ እጥረት ላለባቸው 2ሺህ 199 አጥቢና ነፍሰጡር እናቶች እንዲሁም ከ6ወር እሰከ 5ዓመት የእድሜ ክልል ላይ ለሚገኙ 1ሺህ15 ህጻናት አልሚ ምግብ መሰጠቱን ተናግረዋል።
ኤችአይቪ ኤድስን ለመካከልና ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረትም ለ9ሺህ 453 ሰዎች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የደም ምርመራ አገልግሎትመሰጠቱን ቫይረሱ በደማቸው ለተገኘባቸው 275 ወገኖች ደግሞ የጸረ ኤች አይቪ መድሀኒት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት ከአካባቢው ጋር ተስማሚ የሆኑ ምርጥ የሰብል ዝርያዎችን በ8ነጥብ5 ሄክታር የማባዛት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
እንዲሁም በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ባለፉት ስድስት ወራት ክልሉን ከጎበኙ 3ሺህ የውጭ ሀገራትና 12ሺህ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ከ6 ነጥብ3 ሚሊዮን ብር በላይ የተገኘ ሲሆን ይህም ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የቱሪስቶቹ ቁጥር በ16 በመቶ ገቢው ደግሞ በ7 በመቶ ማደጉን መናገራቸውን የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘገባ ያመለክታል።