የፌደራልና የክልል አፈ ጉባኤዎች ሀገር አቀፍ የጋራ መድረክ ምክክር ነገ በጅጅጋ ከተማ ይካሄዳል

ጅጅጋ መጋቢት 18/2000/ዋኢማ/ የፌዴራልና የክልል ምክርቤቶች አፈ ጉባኤዎች ሀገር አቀፍ የጋራ መድረክ ምክክር ነገ በጅጅጋ ከተማ እንደሚካሄድ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስታወቁ።

አፈጉ ባኤው አቶ መሐመድ ኢሳቅ እንዳስታወቁት፤ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤትና የሁሉም ክልል አፈ ጉባኤዎችና ምክትል አፈ ጉባኤዎች፣ የጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና ከፍተኛ ኤክስፐርቶች በሚሳተፉበት በዚሁ የጋራ መድረክ የምክር ቤቶቹ ያለፉት ስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል።

ምክር ቤቶቹ በህገ መንግስቱ በተሰጣቸው ህግ የማውጣትና የመቆጣጠር ስልጣን ያከናወኗቸው ተግባራት የሚገመገም ሲሆን በተለይ የፌዴራልና የክልሎች ከፍተኛ የስልጣን እርከን የሆኑት ምክር ቤቶቹን አቅም ለማጠናከር በተከናወኑ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚወያይ ገልጸዋል።

በተጨማሪ የጋራ ውይይቱ የየክልሉ ምክር ቤቶች ጠቃሚ አሰራሮችና ተሞክሮዎች ልምድ ለመለዋወጥና የቀጣዩ የምክር ቤቶቹ የትኩረት አቅጣጫ ዙሪያ እንደሚነጋገር አፈ ጉባኤው አስታውቀዋል።

የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ለሶስት ቀናት የሚቆየውን ውይይት ካጠናቀቁ በኋላ በሱማሌ ክልል በመከሄድ ላይ የሚገኙ የልማት ስራዎች ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ መሐመድ ማስታወቃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።