ቢሮው የትምሀርት ጥራትን ለመጠበቅና የመምህራ ዓቅም ለማሳደግ ስልጠና እየሰጠ ነው

ጅጅጋ መጋቢት 18/2000/ዋኢማ/ የሱማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምሀርት ጥራትን ለመጠበቅና የመምህራ ዓቅም ለማሳደግ የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ።

የቢሮው ኃለፊ አቶ በሽር ሼክአብዱራህማን በክልሉ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘውን የትምህርት ጥራት ለማሳደግና የመምህራንን ብቃት ለማጎልበት በ6 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የተለያዩ የዓቅም ግንባታ ተግባራት እያከናወነ ነው።

በዚህ መሰረት ስርተፍኬት ያላቸውን ወደ ዲፕሎማ፣ዲፕሎማ ያላቸውን ደግሞ ወደ ዲግሪ ለማሳደግ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት 600 መምህራን እየሰለጠኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ቢሮው በተያዘው ዓመት 894 የአንደኛ ደረጃ መምህራንና 60 የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ቀጥሮ ማሰማራቱን ገልፀዋል።

በክልሉ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘውን የትምህርት ሽፋን ለማሳደግም ከመደበኛ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ አማራጭ መሰረታዊ ትምህርት መስጫ ተቋማት እየተገነቡ መሆናቸው ኃላፊው መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።