ኢትዮጵያ ለትምህርት ዘርፍ የ70 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ከዓለም ባንክ እንደምታገኝ ሚኒሲቴሩ አስታወቀ

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2000 ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2010 በትምህርቱ ዘርፍ ለማከናወን ላቀደቻቸው ተግባራት ማስፈጸሚያ የሚውል የ70 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ የዓለም ባንክ የትምህርት ለሁሉም ፋስት ትራክ ኢኒሼቲቭ ማስታወቁን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ትናንት ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ኢኒሼቲቩ ኢትዮጵያ በትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ የሀገሪቱን የትምህርት ሁኔታ መለወጥ የሚያስችል መሆኑን ተገንዝቧል። ኢትዮጵያ በትምህርቱ ዘርፍ ለማከናወን ላቀደቻቸው ተግባራት ማስፈጸሚያ የሚውል የ70 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ የድርጅቱ የድጋፍ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሚስተር ጆይ ፋማፊ አረጋግጠዋል።

በሀገሪቱ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ የሚለውን የሚሌኒየሙን የትምህርት ግብ ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራትና በአጭር ጊዜ የተመዘገበው ውጤት ሀገሪቱ ለቀየሰቻቸው የትምህርት ማስፋፋትና ጥራት የማስጠበቅ አቅጣጫዎች ማሳያ መሆናቸውን ኢኒሼቲቩ መጥቀሱን ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

ሚኒስቴሩ እንዳለው ኢትዮጵያ ከጋና ጋር በመሆን አፍሪካን ወክላ በፋስት ትራክ ኢኒሼቲቩ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ናት። ሀገሪቱ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነቷ ሀብታም ሀገሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለታዳጊ ሀገሮች ትምህርትና ሥልጠና መስፋፋት እንዲሁም ጥራት ማስጠበቅ የሚሆን ድጋፍ እንዲያደርጉ በንቃት ትሳተፋለች።

አሁን የተሰጠው ድጋፍ ባለፉት ዓመታት አፈፃፀም ላይ የተመሠረተ መሆኑንና ወደፊትም ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚደረግ መግለጫው አመልክቷል።

አዲስ ዘመን