በክልሉ ዲማ ወረዳ 9 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ የተለያዩ የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸው ተገለጸ

ጋምቤላ መጋቢት 18/2000/ዋኢማ/ በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ 9 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተለያዩ የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ አስታወቁ።

አስተዳዳሪው አቶ ኡጁሉ አደይ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በወረዳው በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚከናወኑት የልማት ሥራዎች የትምህርት፣ የውሃ፣ የግብርናና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ይገኙበታል።

እየተከናወኑ ካሉት የልማት ሥራዎች መካከል 80 ኪሎ ሜትር የበጋና ክረምት የጠጠር መንገድ ጠረጋ፣ የአራት አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት ቤት ፣ የአንድ የገበሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከል፣ አንድ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ የወረዳው ምክር ቤትና ገንዘብና ኢኮኖሚ ጽሕፈት ቤት ግንባታ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

በተለይ የወረዳው ምክር ቤትና ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤቶች ግንባታ 85 በመቶ መጠናቀቁን ጠቁመው፤ ቀሪው ሥራም በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ገልፀዋል።

የመንገዱ መገንባት ወረዳውን ከሌሎች አጐራባች ወረዳዎችና በወረዳው የሚገኙ ቀበሌዎችን እርስ በርስ በማገናኘት በወረዳው የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማፋጠን ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው አስታውቀዋል።

የትምህርት ቤቶች መገንባት በሚሌኒየሙ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት እንደሚያጠናክር ጠቁመው፤ የጽሕፈት ቤቶች ግንባታም የወረዳውን የቢሮ ችግር በማቃለል ለሠራተኛው ምቹ የሥራ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል አቶ ኡጁሉ መግለጻቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።