በዞኑ ዘንድሮ ከ260 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጣቸው

ደሴ መጋቢት 18/2000/ዋኢማ/ በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ዘንድሮ ከ260 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 106 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን የዞኑ ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

የፅህፈት ቤቱ የኢንቨስትመንት ባለሙያ አቶ ጌቱ መንግስቱ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፣ በዞኑ በ25 የገጠርና የከተማ ወረዳዎች 262 ሚሊየን 763ሺ ብር ካፒታል ላስመዘገቡና በልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለሚሰማሩ 106 ባለሀብቶች ፍቃድ ተሰጥቷል።

ባለሀብቶቹ ፈቃዱን የወሰዱት በአበባ ልማት ፣ በደጋ ፍራፍሬ ልማት፣ በወተት ማቀነባበር በቅመማ ቅመም ዘር ምርት፣ በመኖሪያ ቤት ልማት፣ በሆቴልና ቱሪዝም ፣በትምህርትና ጤና ኮሌጅ ግንባታ የሚሳተፉ ናቸው።

በዞኑ ከ1987 ዓም ጀምሮ እስከ 1999 መጨረሻ ለ58 ባለሀብቶች ብቻ ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት ስድስት ወራት 106 ለለሀብቶች ፈቃድ መውሰዳቸው የዞኑ የኢንቨስትመንት ፍሰት እያደገ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል።

የባለሀብቶች ተሳትፎ ካለፉት ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣው ቀደም ሲል በክልል ደረጃ ይሰጥ የነበረው የኢንቨስትመንት ፈቃድ በዞን ደረጃ መስጠት በመጀመሩና በሚሊኒየሙ ሰፊ ህዝባዊ የልማት መነቃቃት በመፈጠሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህ ዓመት ፍቃድ የተሰጣቸው ፕሮጀክቶች ስራ ሲጀምሩ ከ9ሺ 480 በላይ የሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዚያዊ የስራ እድል የሚጥሩ ሲሆን መንግስት የገጠርና የከተማውን አካባቢ ለማልማት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዙም አቶ ጌቱ ተናግረዋል።

በተጨማሪ በማደግ ላሉ ወረዳዎችና ከተሞች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አሰተዋፅኦ እንደሚኖራቸው መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።