ኦህዴድ የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማሳካት ብቃት ያለው ድርጅትነቱን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አስታወቁ

አዳማ መጋቢት 18/2000 የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማሳካት ብቃት ያለው ድርጅትነቱን በተግባር እያሳየ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በአዳማ ከተማ መስቀል አደባባይ ኦህዴድ የተመሰረተበት 18ኛ ዓመት በዓል ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፤ ኦህዴድ በኢህአዴግ ማእቀፍ ውስጥ በመሆን የመላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሕዳሴ ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው።

ኦህዴድ ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጋር በመሆን በቀየሰው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፕሮግራምና መሥመር እየተመራ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ማኒስትሩ፤ ድርጅቱ በኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ አዲስና ገናና ምዕራፍ ለመክፈት መቻሉን አስታውቀዋል።

የኦሮሞ ሕዝብ በእራሱ ቋንቋ በመጠቀምና በመዳኘት ባህሉንና ታሪኩን ለማክበር ከአካባቢው እራሱ በመረጣቸውና ከአብራኩ በተገኙ መሪዎች በመተዳደር በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የተቀናጀ ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት የታገለላቸው የእኩልነትና የራስን እድል በራስ የመወሰን መብቶች በኦህዴድ እና ኢህአዴግ አመራር እንዲሁም በህዝቡ ትግል በተሳካ ሁኔታ ለመረጋገጥ ችሏል ብለዋል።

የኦሮሞ ሕዝብ በኦህዴድ አመራር የታገለላቸውን የፖለቲካ አላማዎች እያሳካ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ይህም ለኢትዮጵያ ሕዳሴ ሁነኛ ግብዓት ሆኖ ለልማቱ መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኦሮሞ ሕዝብ የታገለላቸው የኢኮኖሚ አላማዎች በሚያበረታታ ሁኔታ ተግባራዊ መሆን መጀመራቸውን አስገንዝበዋል።

ኦህዴድ የኦሮሞ ህዝብን ከዳር-ዳር በማነሳሳት በተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ በንቃት እንዲሳተፍና በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻሉን አመልክተዋል።

የኦሮሞ አርሶ አደሮች የግብርና ምርትን በማሳደግና ከልማቱ በተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የግል ኢንቨስትመንት በክልሉ በሰፊው እንዲስፋፋ በማድረግ የክልሉ ከተሞችም በልማቱ እንዲጠቀሙ አድርጓል ብለዋል።

ሕዝቡ የታገለላቸው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ዓላማዎች በኦህዴድ መሥመርና ትግል መሳካት መጀመራቸውን አመልክተው፤ እነዚህም ድርጅቱ ሲመሠረት ጀምሮ ያስቀመጣቸው ግቦች እንደነበሩ አረጋግጠዋል።

ኦህዴድ በጥቂት ታጋዮች መመሥረቱን አስታውሰው፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዓላማዎቹን እያሳካ ያለው ሚሊዮኖችን ከጎኑ በማሳለፍ መሆኑን ገልጸዋል። ከ18 ዓመታት በፊት የተመሠረተው ኦህዴድ በሂደት አንድ ሚሊዮን አባላትና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ማፍራቱን አብራርተዋል።

መንፈሰ ደካሞችን በየምዕራፍ እያራገፍን በታጋዮች መስዋእትነት እየከፈለ ባካሄደው ትግል ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።

የኦሮሞን ህዝብ በህዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባውን በመፈቃቀር ላይ የተመሠረተውን አንድነት በመናድ ለጥቅማቸው የተነሱ ኃይሎችን በመቃወም የቆመ ድርጅት መሆኑን አብስሯል ብለዋል።

ኦህዴድ በተለያዩ መንገዶች የተከፈቱበትን ፀረ-ህዝብ ተግባሮች በመቋቋምና ተገቢውን ምላሽ በመስጠት በጽናት ሲሰራ መቆየቱን አመልክተው፤ በሂደቱም ትክክለኛ መሥመሩን እያጠራና እያጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

የኦህዴድ ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላዠው እንዳስታወቁት፤ ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ ትግል ትክክለኛ መሥመር አስይዞ ኦሮሞነት ክብርና ሞገስ መሆኑን በማረጋገጥ ባስገኘው ድል በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፏል።

ድርጅቱ በከባድ መስዋእትነት ያረጋገጣቸውን መሠረታዊ ድሎችንና የተጀመረውን የእድገት ጉዞ ለማደናቀፍ የሚፍጨረጨሩ ኃይሎችን በቁርጠኝነት መታገሉን ገልጸው፤ ሕዝቡም በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በልማትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኦህዴድ ከህዝቡ ጋር በመሆን ባስመዘገባቸው ድሎች በመበረታታት የገነባው ድርጅታዊ ጥንካሬ መላውን የኦሮሞ ህዝብ የፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ግንባታው ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል።

በእለቱ 18ኛውን የኦህዴድ የምስረታ በዓልን አስመልክተው፤ ያላቸውን ክብር ለመግለጽ የአዳማ ህዝብና መላው የኦሮሞ ህዝብ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንድ በባህላዊ አልባሳት ያጌጠ ሰንጋ ፈረስና ሁለት ኮርማ በሬዎችን በሽልማት አበርክተውላቸዋል። በተጨማሪም የኦሮሞ ባህላዊ ልብስ ከክልሉ ርእሰ መስተዳድር እጅ ተቀብለዋል።

በበዓሉ ላይ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ ከየወረዳው የተወከሉ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች የበዓሉ ታዳሚዎች ነበሩ።

አዲስ ዘመን