አዲስ አበባ መጋቢት 18/2000 ዋኢማ/ ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነ ዓለም ዓቀፍ ጅውሽ ቮይስ ሚኒስትሪ የተባለ ድርጅት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች የነጻ ህክምና በመስጠት ላይ መሆኑን የድርጅቱ ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አሰታወቁ።
የድርጅቱ ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ጆናታን በርኒስ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ የድርጅቱ ህክምና ቡድን በአዲስ አበባና ጎንደር ከተሞች በሚሰጠው አገልግሎት ከ14ሺ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
የህክምና ቡድኑ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ በፍሪ ሜቶዲስት የህክምና ማዕከል አገልግሎት መስጠት በመጀመር እስካሁን ስድስት ሺ የሚሆኑ ነዋሪዎች የተለያዩ የህክምና አገልግሎት መስጠቱን ጠቅሰው፣ በቀሪዎቹ ሁለት ቀናት ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውንና አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ድርጅቱ በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባ ከሚያከናውነው የህክምና አገልግሎት በተጨማሪ በጎንደር ከተማ በተመሳሳይ ሁኔታ ከሰባት ሺ በላይ ለሚሆኑ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን አመልክተው፣ ለተግባራዊነቱ 16 ሚሊየን ብር መመደቡን ተናግረዋል።
ድርጅቱ በአዲስ አበባና ጎንደር ከተሞች ነዋሪዎች ከሚሰጠው አገልግሎት መካከል የአይንና የጥርስ ህክምና፣ የቀዶ ጥገናና የህጻናትና እናቶች ህክምና እንደሚገኙበት ዶክተር ጆናታን አመልክተዋል።
ድርጅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በህንድ፣ ራሽያ፣ አርጀንቲና ዩክሬንና ሌሎችም በርካታ የዓለም አገራት ተመሳሳይ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን አመልክተው፣ በኢትዮጵያ ህብረተሰቡ ተከታታይ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን በማሰብ በዘንድሮው የፈረንጆች ዓመት በአዲስ አበባ ቋሚ የህክምና ማዕከል መስጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል።
የህክምና ቡድኑ ወደ አገር እንዲመጣ ሁኔታዎችን ያመቻቸው የብሩህ ተስፋ ድርጅት ዳይሬክተር ፓስተር ዶክተር ጌታሁን ነሲቡ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ የተለያዩ የህክምና ቡድኖች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የሰብዓዊ ተግባራት እንዲፈጽሙ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመው፤ ከአሜሪካ የመጣው የህክምና ቡድን በሚሰጠው ሰብዓዊ ተግባር ከፍተኛ የህክምና ወጪ መሸፈን የማይችሉት ተጠቃሚ በመሆን ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የህክምና ቡድኑ በአዲስ አበባ እንዲሁም በጎንደር የሰብዓዊ አገልግሎት እንዲሰጥ የተለያዩ የመንግስት አካላት አስተዋጽኦ ማደረጋቸውን ተናግረዋል።
ከአሜሪካ የመጣውና 80 የህክምና ባለሙያዎችን ያካተተው የህክምና ቡድን ስፔሻሊስቶች፣ ዶክተሮች፣ የጤና መኮንኖችና ነርሶችን እንደሚገኙበት ፕሬዚዳንቱ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።