የቤቶች ልማት ፕሮግራሙ ከ59 ሺ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጠረ

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2000/ዋኢማ/ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የተቀናጀ የቤቶች ልማት ፕሮግራም ከ59 ሺ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን የከተማዋ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በትሩ ላቀው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ እስካሁን ከቤቶች ልማት ጋር በተያያዘ 59ሺ 87 የከተማዋ ነዋሪዎች በማህበራት ተደራጅተው ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል አግኝተዋል።

በተያዘው ዓመት በቤቶች ልማቱ ለ56 ሺ 200 ሰዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ በ2ሺ 887 ብልጫ ያለው የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አመልክተዋል።

ከስራ ዕድል ተጠቃሚዎቹ መካከል 27 ሺ 760 ያህሉ ሴቶች መሆናውንቶ በትሩ ጠቁመው፤ ከ41ሺ የሚበልጠው የስራ ዕድል የተፈጠረው በስራ ተቋራጮች መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

የቤቶች ልማት ፕሮግራሙ የቤት እጥረትን ከማቃለል በተጨማሪ በግንባታው ሂደት ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ገቢያቸውን የማሳደግ ዓላማ እንዳለው የገለጹት አቶ በትሩ፤ በዚህም ዜጎች በግንባታ ቁሳቁስ ማምረትና አቅርቦት እንዲሁም በግንባታ ስራ በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከቤቶች ልማት የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሆኑት ዜጎች በ766 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው በመስራት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከኢንተርፕራይዞቹ 546 ያህሉ በግንባታ ቁሳቁስ ምርት ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ለኢንተርፕራይዞቹ የመስሪያ ቦታ፣ ብድርና ስልጠና በመስጠት አቅማቸውን የማጠናከር ስራ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።