የውቅሮ ጋብዮን ፋብሪካ ከ16 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

መቀሌ መጋቢት18/2000/ዋ ኢማ/ በትግራይ ክልል የውቅሮ ጋብዮን ፋብሪካ ባለፉት ስምንት ወራት ለገበያ ካቀረበው ከ90 ሺ በላይ የጋብዮንና ማትረስ ምርቶች ከ 16 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ተክላይ ገብረእግዚአብሄር ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ ፋብሪካው ጋብዮንና ማትረስ የተባሉ ምርቶችን አምርቶ በማሰራጨት ለአካባቢ ጥበቃና ለግብርናው ክፍል ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል።

የፋብሪካው ምርቶች በዋናነት ለአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ ለመሬት መሸርሸር መከላከያ፣ ለወንዝ ጠለፋ፣ ለመንገድና ድልድይ ስራዎች እንደሚውሉ የገለጹት ስራ አስኪያጁ፤ በጋብዮን የዳኑ መሬቶች አፈርና ውሃን ከመጠበቅ አልፈው የከርሰ ምድር ውሃን በማቆር በመስኖ ልማት በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንዳደረጉ አመልክተዋል።

በክልሉ ደቡባዊ፣ ምስራቃዊና ማዕከላዊ ዞኖች ራማ ፣ሴሮ፣ውቅሮ አካባቢዎች እንዲሁም በአላማጣ ከተማ ዙሪያ በጋብዮን ምርት የተሰሩ የውሃ ተፋሰሶች፣ ድልድይና የጎርፍ መከላከያ ውጤታማ መሆናቸውን የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ፣ ይህም ህብረተሰቡና መንግስት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያደረጉ ያሉትን ጥረት ያጠናክረዋል ብለዋል።

የጋብዮንና ማትረስ ተጠቃሚነትን በማስፋት የተራቆቱ የመሬት ክፍሎችን ለማዳን እንዲቻል ፋብሪካው ባለፉት ጥቂት ወራት ከአማራ ክልል 112 ወረዳዎች ለተውጣጡ የግብርና ባለሙያዎች አውደ-ጥናት ማዘጋጀቱንና ጥረቱ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን የክልተ አውላዕሎ ወረዳ ገማድ ቀበሌ ገበሬ ማህበር አርሶ አደሮች መካከል ቅብአቱ ኪሮስና ገብረጻድቃን ሃይለስላሴ በሰጡት አስተያየት ሃይለኛ ጎርፍ ባስከተለው የድንጋይና የአፈር ናዳ ከጥቅም ውጭ ሆኖ የነበረው ማሳና የከብቶች መዋያ በጋብዮን መከላከያ ከተሰራለት በኋላ ለከብቶች መኖ የሚውል ሳር በዓመት ሶስት ጊዜ በማጨድና መስኖ በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከሶስት ዓመታት በፊት በ10 ሚሊየን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመው የውቅሮ ጋብዮን ፋብሪካ በዓመት ሶስት ሺ ቶን የብረት ጥሬ ዕቃ በመጠቀም ከ 200 በላይ የተለያየ መጠን ያላቸው የጋብዮንና የማትረስ ምርቶችን የማምረት ዓቅም እንዳለው ገልፀዋል።

ፋብሪካው ከተቋቋመ ወዲህ ባመረታቸው ከ460 ሺ በላይ ጋብዮኖች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚከሰተውን የመሬት መሸርሸር አደጋ ለማዳን የቻለ ሲሆን፤ ለ150 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል እንደፈጠረ መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።