አዲስ አበባ መጋቢት18/2000/ የአፍሪካ ህብረት በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት በሚያደርገው እንቅሰቃሴ ለሽግግር መንግስቱ ፖሊስ ኃይል ማጠናከሪያ ከጣሊያን መንግስት የ40 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ማግኘቱ ተገለፀ።
አፍሪክ ኦንግሊን የተባለውን ድረ- ገጽ ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደዘገበው፤ የአፍሪካ ህብረት በሶማሊያ ሰላምን ለማስፈን ለሚያደርገው ጥረት ከኢጣሊያ-አፍሪካ የሰላም ፈንድ ድጋፍ አግኝቷል።
በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ በተካሄደው ሥነ ስርዓት ላይ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሮማኖ ፕራዲ ተወካይ ሚስተር አርማንዶ ሳንጉኒ እንደገለጹት፤ መንግስታቸው በአሁኑ ጊዜ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሚያስችል የተመቻቸ ሁኔታ በመፈጠሩ ለሀገሪቱ ፌደራል መንግስት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
የአፍሪካ ህብረትና የኢጣሊያ-አፍሪካ ሰላም ፈንድ ከዚህ በፊት በሰላም ጉዳዮች ላይ አብረው ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን የጠቆሙት ተወካዩ፤ መንግስታቸው የአፍሪካ ህብረት በአፍሪካ ያሉትን ፖለቲካዊ ችግሮችን ለማፍታት የሚያስችለውን የገንዘብ ድጋፍ ማዘጋጀቱን አመልክቷል።
በሶማሊያ ያለው ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በህብረቱ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ በመሆኑና የሀገሪቱ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ሁሉንም ያካተተ የሰላም ውይይት እንዲካሄድ የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ ድጋፍ መደረጉን ተወካዩ ጨምረው አብራርተዋል።
እንደ ሚስተር ሳንጉኒ ገለፃ፤ የጣሊያን መንግስት ከረጅም ዓመታት በኋላ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት በአሁኑ ጊዜ ተሰፋ ሰጪ ሁኔታ መፈጠሩን ተገንዝቧል።
በጣሊያን መንግስት የተሰጠው የገንዘብ ድጋፍ በአፍሪካ ህብረት በኩል የሶማሊያን ፌደራላዊ መንግስት መዋቅርንና የፀጥታ ኃይሉን ለማጠናከር እንደሚውል ተወካዩ ጠቁመው፤ የዓለም አቀፉ ማህበረስብ የሶማሊያን የሰላም ሂደት እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ህብረትን ወክለው የገንዘብ ድጋፉን የተቀበሉት የህብረቱ ሰላምና ፀጥታ ኮሚሽነር ሰይድ ጃንት በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ህብረት ለሶማሊያ በቂ የፖለቲካ፣ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ ያልቻለበት ሁኔታ እንደነበር ገልጸዋል።
በጣሊያን መንግስት የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ለሌሎች የዓለም መንግስታት አርአያ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኑር ሀሰን ሁሴን በበኩላቸው መንግስታቸው በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ መደሰቱን ገልጸው፤ ከተገኘው ድጋፍ ውስጥ 10 ሚሊየን ዶላር የፖሊስ ኃይሉን ለማስልጠንና ለማደራጀት እንደሚውል ጠቁመዋል።
የሽግግር መንግስቱ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለዓለም ህብረተሰብ በማሳወቅ ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ መሰል ድጋፎች በሀገሪቱ ብሔራዊ ዕርቅን ለማምጣት፣ ልማትን ለማስፋፋትና የስብአዊ ዕርዳታን በአግባቡ ለማዳረስ ያስችላል ብለዋል።
በሀገሪቱ ብሔራዊ ዕርቅ ለማምጣት በሚደረገው እንቅሰቃሴ አወንታዊ ውጤቶች በመመዝገብ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ሁሉንም ያካተተ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ዕቅዶችን በማዘጋጀት ላይ እንደሆኑ መጠቆማቸውን የዜና ምንጩን ዘገባ ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።