አዲስ አበባ መጋቢት 18/2000/ዋኢማ/ በሶማሊያ ሰብአዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የሀገሪቱ ዜጎች ዕርዳታ ለማዳረስ እንዲቻል በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ቡድኖች ያሉባቸውን ልዩነቶች በውይይት መፍታት እንዳለባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ሀላፊ አሳሰቡ። የሽግግር መንግስቱ የዕርዳታ ስርጭቱን ለማፋጠን ከረዲኤት ድርጅቶች ጋር እንደሚሰራ አስታቀ።
የድርጅቱን የዜና ማዕከል ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደዘገበው፤ በሶማሊያ ሰብአዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሶማሊያውያን ዕርዳታውን በአግባቡ ለማዳረስ በሀገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ቡድኖች በውይይት ሰላም ማስፈን ይጠበቅባቸዋል።
በሶማሊያ የሚንቀሳቀሱ ወደ 40 የሚሆኑ የረዲኤት ድርጅቶች በሀገሪቱ ስላለው የዕርዳታ ፍላጎትና በድርጅቶቹ ላይ በሚደርሱ ችግሮች ዙሪያ የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ተከትሎ የመንግስታቱ ድርጅት አስቸኳይ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ሀላፊ ሚስተር ጆን ሆልምስ እንደገለጹት፤በርካታ ሶማሊያውያን አስቸኳይ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ዕርዳታውን ለማዳረስ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የረዲኤት ድርጅቶች ብቻቸውን አዳጋች ይሆንባቸዋል።
በመሆኑም የሀገሪቱን ፀጥታ ማረጋገጥና በረዲኤት ድርጅቶች ንብረት፣ ሠራተኞችና ማዕከላት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲቆሙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ሚስተር ሆልምስ አስታውቀዋል።
በሶማሊያ ሰብአዊ ዕርዳታን ለማዳረስ በሚደረግ ጥረት የሚያጋጥሙትን የፀጥታ ችግሮች በዘላቂነት መፍታት እንዲቻል በፖለቲካው ዘርፍ የሚደረገው ለውጥ መጠናከር እንዳለበትና ተቀናቃኝ ኃይሎች ወደ ሰላም መድረክ መምጣት እንሚገባቸው ሀላፊው ገልጸዋል።
ጥሪውን ተከትሎ የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ለአሜሪካ ድምዕ ሬዲዮ እንግሊዝኛው ክፍል እንደተናገሩት፤ የረዲኤት ድርጅቶች ለሀገሪቱ ዜጎች ሰብአዊ ዕርዳታ ለማዳረስ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያስተጓጉሉ ችግሮችን ለመፍታትና ስርጭቱን ለማፋጠን ከድርጅቶቹ ጋር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ አሉ የሚባሉትን ችግሮች ለማስወገድ አንድ የዕርዳታ ስርጭቱን የማስተባበርና የማቀናጀት ሥራ የሚሰራና የፀጥታ ቁጥጥር የሚያደርግ አካል እንደሚቋቋም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለፃቸውን የዜና ምንጩን ጠቅሶ ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።