ኢህአዴግ በድሬደዋ ጊዜያዊ አስተዳደር በሚካሄደው ምርጫ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን እያከናወነ ነው

ድሬዳዋ መጋቢት 18/2000/ ዋኢማ/የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ በመጪው ሚያዝያ ወር በድሬደዋ ጊዜያዊ አስተዳደር በሚካሄደው የአካባቢና ማሟያ ምርጫ የቅስቀሳና የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

የድሬዳዋ ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አብዲ አቡበከር ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ድርጅቱ ቅስቀሳና የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራቱን እያከናወነ ያለው በሁሉም የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች ውስጥ ነው።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የቅስቀሳ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ድርጅቱ የነደፋቸውን ትክክለኛ ዓላማዎች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በአግባቡ በማስፈፀም ላይ መሆኑንና ከምርጫው በኋላም ስለሚሰሩ ተግባራት ከህብረተሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መድረሱን አመልክተዋል።

በአስተዳደሩ በመጪው ሚያዝያ ወር ለሚካሄደው የአካባቢና ማሟያ ምርጫ ድርጅቱ ያቀረባቸው እጩዎች ለመልካም አስተዳደር መስፈን የሚታገሉ፣በመልካም ሥነ ምግባር የተመሰገኑና ልማትን ለማፋጠን ቆርጠው የተነሱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

እንዲሁም ድርጅቱ ያቀረባቸው ዕጩዎች ወጣቶችን ፣ሴቶችን ፣ምሁራንና ሌሎችንም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉ፣ በትምህርት ደረጃቸውና በአመራር ችሎታቸው ብቃት ያላቸው በመሆናቸው ህብረተሰቡ በመምረጥ እንዲሳተፍ አቶ አብዲ ጥሪ አቅርበዋል።