ለአካባቢና ማሟያ ምርጫ የሚያገለግሉ የምርጫ ሰነዶች መጓጓዝ መጀመራቸውን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

አዲስ አበባ መጋቢት 17/2000/ዋኢማ/ በመጪው ሚያዚያ ወር ለሚካሄደው የአካባቢና ማሟያ ምርጫ የሚያገለግሉ የምርጫ ሰነዶችና ቁሳቁስ መጓጓዝ መጀመራቸውን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በቦርዱ የሎጅስቲክስ አስተባባሪ አቶ ብሩክ ወንድወሰን ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ ከዛሬ መጋቢት 17/2000 ጀምሮ ለአካባቢና ማሟያ ምርጫ ማስፈጸሚያ የሚውሉ ሰነዶችና ቁሳቁስ ወደ ክልሎች መጓጓዝ ጀምረዋል።

ለምርጫው ማስፈጸሚያ የሚያገለግሉ 1ሺ 300 ካርቶን የምርጫ ሰነዶች በትግራይ ክልል ወደሚገኙ 2 ሺ 600 ምርጫ ጣቢያዎች ዛሬ ጥዋት መላካቸውን ገልጸው፤ ወደ አማራ ክልል ደቡብና ሰሜን ጎንደር ዞኖችና ቤኒሻንጉል ጉሙዝም የሚላኩ የምርጫ ሰነዶች ዝግጅታቸው ተጠናቀው በዛሬው ዕለት ተጭነው እንደሚላኩ አስረድተዋል።

በቀጣይም ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመላክ ዝግጅት መጠናቀቁንና ወደ ደቡብ ክልል ሰነዶቹን ለመላክ ዝግጅት መጀመሩን ጠቁመው፤ የየክልሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና በወሰዱበት ዙር መሰረት ሰነዶች እንደሚላኩ አመልክተዋል።

የምርጫ ሰነዶችና ቁሳቁስ ስርጭት የአካባቢና ማሟያ ምርጫ በሚከናወንባቸው ክልሎች በሳምንት ጊዜ ውስጥ ተጓጉዞ እንደሚጠናቀቅ ገልጸው፤ ባጠቃላይ የምርጫ ማስፈጸሚያ ሰነዶችና ቁሳቁስ የያዙ ከ20ሺ በላይ ካርቶን መዘጋጀቱንና የተጠናከረ ጥበቃ አንደሚደረግላቸው ገልጸዋል።

በቀጣዩ ወር ውስጥ የአካባቢና ማሟያ ምርጫ የበሚካሄድባቸው 780 የወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ከ41ሺ 600 በላይ የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን አስተባባሪው አመለክተዋል።

የተላኩት ሰነዶች የቁጥር ስህተት ቢኖራቸውና የሚበላሹ ሰነዶች ካሉ ለመተካት የሚያስችል መጠባበቂያ ልዩ ልዩ ሰነዶች አብረው እንደሚላኩና ተሰባሪ ቁሳቁስ ስላሉ ለነዚህ መጣበቂያ የሚሆኑ ሁለት ሁለት ካርቶኖች ለየምርጫ ጣቢያዎች በተጨማሪ እንደሚላክም አብራርተዋል።

ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላም ውጤቱን አጠናክረው የሚልኩበት ሰነድና የኮሮጆ ቁልፍ ቢሰበር እንዲሁም የቁጥር ስህተት ቢኖር በሚል የተሰጣቸውን መጠባበቂያ የምርጫ አስፈጻሚዎች በአግባቡ እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።

በቀሩት ጥቂት ቀናት ውስጥ ሰነዶች በየምርጫ ጣቢያው ተሰራጭተው እንዲጠናቀቁ የዞንና ወረዳ አስተዳደር ኃላፊዎች ተሽከርካሪ በማቅረብ የተለመደ ትብብራቸውን እንዲሰጡ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።