አሶሳ መጋቢት 17/2000/ዋኢማ/ የኢትዮጵያ ብድርና ቁጠባ ተቋም በቀጣይ ሶስት ዓመታት ውስጥ የሚሰጠውን የብድር መጠን ወደ 10 ቢሊየን ብር ለማሳደግና የተበዳሪውንም ቁጥር 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ለማድረስ ማቀዱን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማህበር ዳይሬክተር ዶክተር ወልዳይ አማሐ ለዋልታ ኢንፎርሜሸን ማዕከል እንደገለጹት፤ ህብረተሰቡ ራሱን በማህበራት በማደራጀትና የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር በድህነት ቅነሳ ውስጥ የሚያደርገውን ሚና ለማጐልበትና ያለበትን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ እስከ 10 ቢሊየን ብር በብድር ለመስጠት ታቅዷል።
ተቋሙ የህብረተሰቡን የብድር ፍላጐት፣ የሥራ ተነሳሽነትና የመንግስትን የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ መሠረት በማድረግ በሚሰጠው ብድር በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡም የቁጠባ ባህሉን አዳብሮ ልማትን ለማሳደግ እንድያውለው ለማድረግም 3 ቢሊየን ብር ከተበዳሪዎች ለመቆጠብ መታቀዱን የገለፁት ዶክተር ወልዳይ፤ አሁን ያሉት 28 ቅርንጫፎች ጽሕፈት ቤቶችን የማስፋፋትና አቅማቸውን የማጐልበት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
መንግሥት ተቋማቱን ለማሳደግ እያደረገ ያለው እገዛ እጅግ አመርቂ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተቋማቱም ከመንግስት የግብርና፣ የድህነት ቅነሳና የመልካም አስተዳደር ስራዎችና ፖሊሲዎች ጋር ተቀናጅተው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአገሪቷ የሚገኙት የብድርና ቁጠባ ተቋማት በአሁኑ ወቅት ግማሽ ሚሊየን ለሚሆኑ ደንበኞች ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ እያበደሩ መሆናቸውን ከተሰጠው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።