በዞኑ በተለያዩ ሰው ሰራሽ ችግሮች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ከ9ሺ በላይ አባዋራዎች ወደቀያቸው እየተመለሱ ነው

ጋምቤላ መጋቢት 17/2000/ዋኢማ/በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን በተለያዩ ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ከ8 ዓመት በፊት ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ከ9ሺ በላይ አባዋራዎችና እማዋራዎች ወደቀያቸው በመመለስ ላይ መሆናቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የከፊል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጓነር የር እንደለገፁት፤ ወደቀያቸው በመመለስ ላይ ያሉት የተመለሱት አባዎራዎችና እማዋራዎች ከ8 ዓመት በፊት በሱዳን የምርሌ የጐሣ አባላት ባካሄዱት ዘረፋና በሌው ኑዌር የጐሣ ግጭት ምክንያት በዞኑ ከሚገኙ ዋንቱዋ፣ አኮቦ፣ ላሬና ጅካዎ ወረዳዎች ተፈናቀለው የነበሩ ናቸው።

ለዓመታት ተፈናቅለው የነበሩት አባዋራዎችና እማዋራዎች ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ የቻሉት በወረዳዎቹ አስተማማኝ ሠላም በመስፈኑና ወደ ቀያቸው ለመመለስ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

አባዋራዎቹንና እማዋራዎቹን የመመለሱ ሥራ የተጀመረው ባለፈው ሳምንት መሆኑን የገለፁት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከ3ሺ የሚበልጡት ወደቀያቸው መመለሳቸውንና ቀሪወቹም እስከ መጋቢት 21/2000 ዓመተ ምህረት ድረስ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀያቸው እንደሚመለሱ አስታውቀዋል።

አባዎራዎቹና እማዋራዎቹ ወደ ቀያቸው መመለሳቸው በጋምቤላና ኢታንግ ወረዳዎች ከግጣሽና ከእርሻ መሬት ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን ግጭት በማስወገድ የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።