በአዳማ ሲካሄድ የቆየው የሁለተኛ ደረጃና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የስፖርት ውድድር ትናንት ተጠናቀቀ

አዳማ መጋቢት 17/2000/ዋኢማ/ የኦህዴድን 18ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ በአዳማ ከተማ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ውድድር ትናንት ተጠናቀቀ።

በስፖርታዊ ውድድሩ የተሳተፉት ስምንት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ስምንት ኮሌጆች ሲሆኑ፤ ከ1 ሺ 50 በላይ ተማሪዎች በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ መረብ ኳስና በብስክሌት የስፖርት ዓይነቶች ተወዳድረዋል።

በመዝጊያ ስነ ስርዓቱ በእግር ኳስ ለዋንጫ የደረሱት የቦሮና የናፍያድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተጫውተው የናፍያድ ትምህርት ቤት የቦሮን ትምህርት ቤትን ሶስት ለሁለት በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል።

በመረብ ኳስም አዳማ ዩኒቨርሲቲ አዳማ ቴክኒክ ሙያ ኮሌጅን ሶስት ለባዶ በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ዋንጫ ሲያገኝ፤ በእግር ኳስ ከጎሮ ትምህርት ቤት ፍጹም ክፍሌ በመረብ ኳስ ከአዳማ ዩኒቨርስቲ መልካሙ ማንዳሮ በኮኮብ ተጫዋችነት ተመርጠው ተሸላሚ ሆነዋል።

በአትሌቲክስ በተደረገ የ10 ሺ ሜትር ሩጫ በወንዶች አልታሰብ አወቀ፣ ኃይሉ ቶሎሳና በለጠ አብዶ ከአንድኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ሲያገኙ በሴቶች አብደኔ አቤቤ፣ ደምቱ ሐዋስና ዝናሽ ብርሃኑ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ በማግኘት አሸናፊ ሆነዋል።

በብስክሌት በተደረገው የ30 ኪሎ ሜትር ውድድር ሰመረዲን አህመድ፣ ኑረዲን ሙሳና ብሩክ ግርማ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት ያሸነፉ ሲሆን፤ በአትሌቲክቱ ስፖርት አሸናፊ ለሆኑት ስፖርተኞች እንደየደረጃቸው እስከ 750 ብር የገንዘብ ሽልማት ተሰቷል።

የአዳማ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን በንቲ የኦህዴድ 18ኛ ዓመት የምስራታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የነበረው የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር በተሳካ መልኩ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ያለው የእግር ኳስ ፕሮጀክት ስልጠና በከተማዋ ጥሩ ስፖርተኞችን ለማፍራት እያስቻለ መሆኑን ለመመልከት ተችሏል ያሉት አቶ ሁሴን፤ ጽህፈት ቤቱ የከተማዋን ስፖርት ለማሳደግ ጥረት እንደሚያደርግ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።