አዲስ አበባ መጋቢት 16/ዋኢማ/ የአትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ኮርፖሬሽን ብዛት ያላቸው ደንበኞችን በአጭር ጊዜ ለማስተናገድ የሚያስችል ዘመናዊ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት እየዘረጋ መሆኑን አስታወቀ።
በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱራሂም አህመድ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ አዲስ በመዘርጋት ላይ ያለው ሥርአት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የተጋነነ ክፍያን ያስቀራል።
በማዞሪያ በኩል የሚመጡ የተለያዩ መልክቶችና መረጃዎች መድረሳቸውን የሚያረጋግጥ የመሳሪያ ተከላ ሥራም እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሥራው ሲጠናቀቅ በአከፋፈልና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው አሠራሮች ላይ መሻሻል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ በአገልግሎት አከፋፈል ዙሪያ የተለያዩ አቤቱታዎችን ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰው፣በዘንድሮው የበጀት አመት በርካታ የማሻሻያ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥ በመዘርጋት፣በማስፋፋትና በማጠናከር አዳዲስ ደንበኞችን ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ ኮርፖሬሽኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንና የተጋነነ ቢል የሚመጣበትን የክፍያ ሁኔታ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።