የመታሰቢያ ሐውልቱ ሰማዕታቱ የተዋደቁለትን ክብር ዓለማ ከግብ ለማድረስ የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ተገለጸ

አዳማ መጋቢት 17/2000/ዋኢማ/ የኦሮሞ ታጋዮች መታሰቢያ ሐውልት የትጥቅ ትግሉ የነበረውን ፀረ ጭቆና ፍልሚያ የሚዘክር ብቻ ሳይሆን ሰማዕታቱ የተዋደቁለትን ክብር ዓላማ ከግቡ ለማድረስ በሁሉም የልማት መስኮች ጠንክረን እንዲንረባረብ የቃል ክዳን ማደሻ ማዕከል ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አስታወቁ፤ የመታሰቢያ ሐውልቱን ለመገንባት ከ63 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል።

ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በአዳማ ከተማ የተገነባውን የኦሮሞ ሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት ትናንት መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የለሕዝብ መብትና ክብር ሲሉ ውድ ሕይወታቸውን የሰው ጀግኖችን ለዘላለም በማስታወስ የወደቁለትን ዓላማ ከግቡ ለማድረስ ሁሉም በልማት መስኮች በመረባረብ የፀረ ድህነት ትግሉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ሰማዕታቱ የጭቆናውን አገዛዝ ገርስሰው ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደተዋደቁ ሁሉ አሁን ያለው ትውልድም አርአያቸውን ተክተሎ ራሱንና ሀገሩን ከድህነት ቀንበር ለማላቀቅና ከፍተኛ ገቢ ያላት ሀገር ለመገንባት ከመቼውም በበለጠ መልኩ መንቀሳቀስ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

የብሔር ብሔረሰቦችን መብቶች ያረጋገጠው ሕገ-መንግስትም ሆነ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን የሰፈነው የሰላም፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውጤቶች የተሰውት የጀግኖች ልጆቻችን ደም ውጤት መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ የእነዚህን ቀጣይነት በአዲሱ ሚሌኒየም ለማረጋገጥ ሁሉም በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው የተሰውት የኦሮሞ ታጋዮች የኦሮሞ ሕዝብ የተነጠቀውን ብሔራዊ መብቶቹን እንዲቀዳጅ ለማስቻል መሆኑን ጠቅሰው፤ ሕዝቡም ዓላማውን ከግቡ ለማድረስ በሁሉም መስኮች አንድነቱን አጠናክሮ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በጋራ መንቀሳቀስ እንደለበት አስታውቀዋል።

የአህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ዘላለም ጀማኔ የሐውልቱን ግንባታ አስመልክተው ባቀረቡት ሪፖርት የኦሮሞ ሕዝብ የብዙ ዓመታት ጥያቄዎችን ለመመለስ ለተሰውት ጀግኖች መታሰቢያ ሐውልት ታሪኩንና ዘመናዊነቱን ጠብቆ እንዲገነባ ከ63 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህም ውስጥ 23 ነጥብ 4ቱን ሚሊየን ብር የሀገር መከላከያ ሰራዊት መሸፈኑንና ቀሪውን ደግሞ ዶክተት ሼህ መሐመድ አላሙድን መመደባቸውን አብራርተዋል።

በሐውልቱ ምረቃ ላይ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስንና የኢፌዴሪ ግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሰን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።