ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዕገዛ ከፍተኛ መሆኑን ቀዳማዊት እመቤት ገለፁ

ባሕር ዳር መጋቢት 16/2000/ዋኢማ/በአገሪቱ ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግሥት እያደረገ ካለው ጥረት ጎን ለጎን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣የኃይማኖት ተቋማትና ማኅበራት የሚያደርጉት ዕገዛ ከፍተኛ አቅም እየፈጠረ መሆኑን የብሐራዊ ፀረ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ የሴቶች ጥምረት ሊቀመንበር ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን ገለጹ።

ሴቶች በአገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ፣ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፎ እንዲያደርጉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አያሌው ጎበዜ አስታውቀዋል።

የጥምረቱ ሊቀመንበር ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን 3ኛው ዙር የአማራ ክልል የፀረ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ የሴቶች ንቅናቄ ማቀጣጣያ የፓናል ውይይት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ሲካሄድ እንደገለፁት፤ ኤች አይ ቪ/ኤድስ በአገሪቱ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለማቃለል መንግሥት የተለያዩ የጤና ፓኬጆችን ቀርፆ በመንቀሳቀስ ላይ ነው።

የኤች አይ ቪ ኤድስ /ቫይረስ አምራች በሆነው ወጣት ላይ ያደርስ የነበረው ከፍተኛ ጉዳት በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እየቀነሰ መመጣቱን የጠቆሙት ቀዳማዊት እመቤት አዜብ፤ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ግን የተፈለገውን ያህል ውጤት እንዳላመጣ ጠቁመዋል።

በተለይ መንግስት ኅብረተሰቡ ራሱን አውቆ ህይወቱን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲመራ ለማስቻል በጀት በመመደብ በሁሉም አካባቢዎች በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የኤች አይ ቪ/ኤድስ የደም ምርመራ ማዕከላትን በማቋቋም አገልግሎቱን ለማስፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ኅብረተሰቡ ስለ ቫይረሱ ያለው ግንዛቤ የበለጠ እንዲጎለብት መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣የኃይማኖት ተቋማትና የተለያዩ ማህበራት በህዝቡ ዘንድ ንቅናቄ ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መሰተዳድር አቶ አያሌው ጎበዜ በበኩላቸው፤መንግሥት በየደረጃው የሚገኙ ሴቶች በአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የማይተካ ሚና እንዳላቸው በመገንዘቡ የሴቶችን መብትና ጥቅም በማስከበር በምጣኔ ሀብታዊ፣ በማኅበራዊና ፖሊቲካዊ ጉዳዮች ተሳትፏቸው እንዲጎለብት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይ በፖለቲካው መስክ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና የአመራር ሰጪነት ሚናቸውን ለማጠናከር በወረዳና በቀበሌ ከሚኖራቸው ተሳትፎ በተጨማሪ በክልልና በፌደራል ደረጃ ውክልናቸው እንዲያድግ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ማህበርና የክልሉ ፀረ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ ሴቶች ጥምረት ''ያልተወለዱ ሕፃናትን እናድን'' በሚል መሪ ቃል ዛሬ ለአንድ ቀን በጋራ ባዘጋጁት ሕዝባዊ ውይይት ላይ በሴቶችና ኤች አይቪ/ አደስ ዙሪያ በአገሪቱ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታና የሌሎች አፍሪካ አገሮች ተመክሮ ያገናዘበ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይቱ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታየ ምናለን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት እንዲሁም ከክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተውጣጡ ከአንድ ሺ በላይ ሴቶችና የአመራር አካላት መሳተፋቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።