አዲስ አበባ መጋቢት16/2000/ ዋኢማ/ በመጪው ሚያዚያ ወር በሚካሄደው የአካባቢና ማሟያ ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን በአግባቡ እያካሄዱ መሆናቸውን በየአካባቢው ያሉ የምርጫ አስተባባሪዎች አስታወቁ። ፓርቲዎቹ ለሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች የምርጫ ቦርዱን ህግ በመከተል ምላሽ እየተሰጣቸው መሆኑ ተገልጿል።
በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምርጫ አስተባባሪ አቶ ደስታ ሀይለሚካኤል ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ በከተማዋ በሚካሄደው ምርጫ ለመወዳደር ዕጩዎቻቸውን ያስመዘገቡ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ቅስቀሳውን በአግባቡ እያካሄዱ ነው።
እስካሁንም የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ባዘጋጀው የክርክር መድረክ ላይ በመገኘት ፓርቲዎች የያዙትን አጀንዳዎችና የልማት አማራጮች በማሳወቅ ቅስቀሳቸውን ያካሄዱ ሲሆን፤ የሚወክላቸውን የምርጫ ምልክትና ፖስተሮችን እየለጠፉ ናቸው ብለዋል።
በቅሰቀሳው ላይ የጎላ ችግር አለማጋጠሙን ጠቁመው፤ ፓርቲዎቹ ለሚያቀርቡት አንዳንድ ቅሬታዎችም የምርጫ ቦርዱን ህገ በመከተል ተገቢው ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን አቶ ደስታ ተናግረዋል።
የጉራጌና የየም ልዩ ወረዳ ምርጫ አስተባባሪ አቶ ፈቀደ መንጀታ በበኩላቸው፤ በዞኑና በልዩ ወረዳው እስካሁን እየተካሄደ ባለው የምርጫ ቅስቀሳ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን የያዙ አጀንዳዎች ለህበረተሰቡ በማስተዋወቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዞኑና በልዩ ወረዳው ኢህአደግ፣ ኢዴህአፓ መድህን፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ህብረትና የወለንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የሚወዳደሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ፓርቲዎቹ ለሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች መፍተሄ እየተሰጠ ነው ማለታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።