ባለስልጣኑ በስድስት ከተሞች የመገበያያ ማዕከላት ስራ እንደሚጀምሩ አስታወቀ

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2000/ዋኢማ/ መንግስት የምርት ገበያን በስርዓት ለመምራት እንዲቻል በወሰደው እርምጃ መሰረት በስድስት ከተሞች የመገበያያ ማዕከላት በቅርቡ ስራ እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን አስታወቀ። በመንግስት እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎችም ዋጋን ለማረጋጋት የጎላ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ የመገበያያ ማዕከላቱን ስራ ለማስጀመር እንዲቻል የተለያዩ የጥራትና ደረጃ መለኪያ መሳሪያዎች እየተሟሉላቸው ይገኛሉ።

የገበያ ማዕከላቱ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት አማካኝነት እየተደራጁ መሆናቸውን የጠቆሙት አምባሳደር አዲስዓለም፤ ማዕከላቱ የተቋቋሙትም በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ነቀምት፣ ቡሬ ጎጃምና ሁመራ አካባቢዎች መሆኑን ተናግረዋል።

በሂደት ባህላዊውን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ስርዓት በዘመናዊ የግብይት ስርዓት ለመተካት በሚደረገው ጥረት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው በታመነበት ተግባር ለሚሳተፉ ግለሰቦችና ነጋዴዎች ዕውቅና እየተሰጠ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የገበያ ስርዓቱ በምርት ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን አለመጣጣም በመቀነስ አምራቹንና ሸማቹን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመልክተው፤ ዝቅተኛውና ከፍተኛው ዋጋ በገበያ አስተዳደሩ ስለሚወሰን ህገ ወጥ ነጋዴዎች እንደፈለጉ ዋጋ የሚጨምሩበትን ዕድል እንደሚያሳጣ አስታውቀዋል።

የገበያ ስርዓቱ ስራ ከመጀመሩ በፊት በተያዘው ወር መጨረሻ ላይ አንድ አገር አቀፍ ጉባኤ እንደሚካሄድ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በጉባኤው ላይ የመንግስት አካላት፣ ማኅበራት፣ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

በተያያዘም በከተሞች አካባቢ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለማርገብ በመንግስት በመወሰድ ላይ የሚገኙት እርምጃዎች ተገቢና ዋጋን ለማረጋጋት ጠቀሚ መሆናቸውን የገለጹት አምባሳደር አዲስዓለም፤ በተለይም ህገ ወጥ የገንዘብ ምንዛሪን ለማስቆም የተወሰደው እርምጃ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ ለመቀነስ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ንግድ ባንኮች የግዴታ ተቀማጭ ገንዘባቸውን እንዲያሳድጉ የሚያደርግ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ መደረጉና በምግብና በምግብ ነክ ምርቶች ላይ የተጣሉ ታክሶች መነሳታቸው ዋጋን ለማረጋጋት የተወሰዱ ጠቃሚ እርምጃዎች መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ህገ ወጦችን ለመከላከል የሚያስችል በግልጽ መረጃ ላይ የተመሰረተ የገበያ ስርዓት ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን እንደሚረዳ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።