ድርጅቱ ሶስት የማይክሮሶፍት ሶሉሽንስ ፕሮግራሞችን አስተዋወቀ

አዲስ አበባ መጋቢት16/2000/ዋኢማ/ "ማይክሮሶፍት ኢስት አፍሪካ ሶፍትዌር ሊሚትድ" የተባለ ድርጅት ለኢትዮጵያ አገልግሎት የሚውሉ ሶስት የማይክሮሶፍት ሶሉሽንስ ፕሮግራሞችን ዛሬ በሸራተን አዲስ አስተዋወቀ።

ድርጅቱ በአገሪቱ ለሚገኙ የአይቲ ቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና ተጠቃሚዎች ያስተዋወቃቸው አዲሶቹ የማይክሮሶፍት ሶሉሽንስ ፕሮግራሞች ዊንዶውስ ሰርቨር 2008፣ ቪዡዋል ስቱዲዮ 2008ና ኤስኪውኤል ሰርቨር2008 ሲሆኑ፤በዓለም አቀፍ ደረጃ ማይክሮሶፍት እያስተዋወቃቸው ካሉት የማይክሮሶፍት ሶሉሽንስ ፕሮግራሞች መካከል መሆናቸውም ተገልጿል።

የማይክሮሶፍት ምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዴቪድ ንዱንጉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፤ አዳዲሶቹ ፕሮግራሞች የተሰሩት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ሥራ አስኪያጆች፣ አስፈጻሚዎችና ባለስልጣናት በአፍሪካ የሶፍትዌር አተገባበርን ለማሳደግ እንዲችሉ ታስቦ ነው።

የቴክኖሎጂዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለሚሰሩና የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ለሚፈልጉ ባለሙያዎች ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመው፤ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች የሚጠቀሙ አጋር ድርጅቶች፣ ደንበኞችና ተገልጋዮች በእያንዳንዱ የቀን ተቀን ተግባራቸው ለውጥ እንደሚያመጣላቸውም ተናግረዋል።

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተሰማሩ ድርጅቶች ሥራቸውን በተዋጣለት መልኩ እንዲያከናውኑና መንግሥትም ለዜጎቹ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጠፋ ለማድረግ እንደሚረዳ አስታውቀዋል።

ፕሮግራሞቹ ከመተዋወቃቸው በፊት በባለሙያዎች አስተያየትና ግምገማ እንደተደረገባቸው ገልጸው፣ከባለሙያዎች የተሰጠው አስተያየትም ለፕሮግራሙ ውጤታማነት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

አዳዲሶቹ ፕሮግራሞች በዓለም ላይ በሚገኙ የአይቲ ባለሙያዎች አስተያየት ተሰጥቷቸው የተሰሩ በመሆናቸው ቀደም ሲል ከተሠሩት የማይክሮ ሶፍት ፕሮግራሞች የተሻሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይ ቪዡዋል ስቱዲዮ 2008 የተባለው ፕሮግራም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የተለያዩ ቋንቋዎች ባሏቸው አገራት ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ዊንዶው ሰርቨር 2008 የተባለው ፕሮግራም ተጠቃሚዎችም መረጃዎችን ለማስቀመጥ፣ ኔትወርክንና የአይቲ ሲስተምስን ለመቆጣጠር እንደሚረዳ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።