የአሜሪካ መንግስት በኤርትራ ያለውን የሰብአዊና ሐይማኖታዊ ጥሰት በመከታተል ላይ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2000/ዋኢማ/ የአሜሪካ መንግስት በኤርትራ ያለውን የሰብአዊና ሐይማኖታዊ መብቶች ጥሰት ትኩረት ሰጥቶ መሆኑን አስታወቀ። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዓለም ላይ የሐይማኖት ነፃነትንና ሰብአዊ መብትን ይገድባሉ ካላቸው አስር ሀገራት መካከል ኤርትራ አንዷ መሆኗን አመልክቷል።

ሚሺን ኔትዎርክ ኒውስ የተባለውን ድረ -ገጽ ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደዘገበው፤ የኤርትራ መንግስት በዓለማችን ላይ የሰብአዊ መብትና የሐይማኖት ነፃነት በከፍተኛ ደረጃ የሚጣስባት ሀገር ናት።

የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰብአዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ባቀረበው አመታዊ ሪፖርቱ ላይ እንዳለመከተው፤ ኤርትራ ሰላማዊ ሰዎችን በሐይማኖታቸው ምክንያት ማሰሯን ቀጥላበታለች።

ኤርትራ ዕውቅና ከሰጠቻቸው ሀይማኖቶች ውጭ የሚገኙ የክርስትና ሀይማኖት ተከታዮችን በሀገሪቱ በሚገኙ ወታደራዊ እስር ቤቶች በማሰርና በመሰቃየት ላይ መሆኗን ዘገባው አመልክቷል።

የሻዕቢያ መንግስት ድርጊቱን ቢክድም በሀገሪቱ የሚገኙ ክርስቲያኖች ሐይማኖታቸውን በነፃነት ለማራመድ እንዲችሉ ከፀጥታ ኃይሎች እይታ ለመሰወር መገደዳቸውን ጠቁሟል።

በተጨማሪም በኤርትራ በአሁኑ ጊዜ ከ ሁለት ሺ በላይ ክርስቲያኖች ኢ-ሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ታስረው የሚገኙ ሲሆን፤ ታሳሪዎቹ በሕግ የመዳኘት መብት መከልከካቸውን የዜና ምንጩ ዘገባ አመልክቷል።

አሜሪካ የኤርትራ መንግስት በሰብአዊ መብትና በሐይማኖት ነፃነት ላይ ገደብ በመጣል በዜጎቹ ላይ በሚፈጽመው ኢሰብአዊ ተግባር በዓለማችን ከሚታወቁ አስር ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ማስገቧቱን ሚሺን ኔትዎርክ ኒውስ የተባለውን ድረ ገጽ ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።