ሐረር መጋቢት 16/2000/ዋኢማ/ በምስራቅ ኢትዮጵያ በሚገኘው የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና መጠለያውን እንደገና ለመከለል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን የፌደራል ግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር ደኤታ አቶ አህመድ ናስር የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያን አስመልክቶ ዘለቄታዊ የዱር ህይወት ልማት የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በሐረር ከተማ ባዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ እንደገለጹት፤ በመጠለያው አካባቢው የሚታዩ ችግሮችን ለዘለቄታው ለማስወገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
በዚህም መሠረት ከፌደራል ግብርናና ገጠረ ልማት ሚኒስቴርና ከሚለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ አንድ ቡድን በመጠለያው በሚገኙ ዝሆኖችና በአካባቢው ፍሎራ ኢኮ ፓወር የተባለ የጉሎ እርሻ ልማት ካምፓኒ በሚካሄደው የኢንቨስትመንት እንቅሰቃሴ ከዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ አንጻር ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ያሉ ችግሮች ማየቱን ገልጸዋል።
በመለጠያው አካባቢ የሚካሄደው የኢንቨስትምንት እንቅስቃሴም ሆነ በመለጠያው የሚገኙ ዝሆኖችና የዱር እንስሳት የአካባቢው ህብረተሰብ ህይወት የሚለውጡና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያሳድጉ በመሆናቸው ሁለቱም ተጣጥመው ሊሄዱ ይገባል የሚል አቅጣጫ መቀመጡን ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።
በአካባቢው የሚካሄደው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ምንያህል የዱር እንስት ጥበቃውን ሊጎዳ አነደሚችል ዝርዝር ጥናቶች ተካሄደው ውይይቶች መደረጋቸውንመ አስታውቀዋል።
በመጠለያው የሚገኙ ዝሆኖችና የዱር እንስሳት ተገቢውን ጥበቃና እንክብኬባ እንዲያገኙ ከባለድርሻ አከላትና ከህብረተሰቡ ጋር የሚደረጉ ውይይቶችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንደተጠናቀቁ መጠለያው እንደገና እንዲካለል እንደሚደረግ አስረድተዋል።
የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ሲሳይ በበኩላቸው፤ የመጠለያው እንደገና መከለል በአካባቢው ዝርያው በመመናመን ላይ የሚገኘውን ብርቅዬ ዝሆኖችንና ሌሎች የእንስሳትና የአእዋፍ ዝርያዎችን ደህንነት ጠብቆ ለማቆየት እንደሚረዳ አመልክተዋል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙ ከፓርኩ አዋሳኝ የሶማሌና የኦሮሚያ ወረዳዎች የውጣጡ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ የተጀመረውን ጥረት እንደሚደግፉና በሥራው ወቅት አስፈላጊውን ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ 6ሺ 982 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ሲኖረው በውስጡ በርካታ ዝሆኖችና ከ250 በላይ አእዋፍና 22 አጥቢ የዱር እንሰሳት እንደሚገኙ ከመጠለያው ጽህፈት ቤት የተገኘውን መረጃ ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።