በውጭ የሚኖሩ የድሬደዋ ተወላጆችና ወዳጆች የሆኑ ኢትዮጵያውያን በድሬደዋ ኢንቨስት ማድረግ ጀመሩ

ድሬዳዋ ጥር 19/2000/ዋኢማ/ በውጭ የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች በከተማዋ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት ጀመሩ። በሚሊኒየሙ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ አንደንድ ኢትዮጵያዊያን ፈቃድ ወስደው የቁም እንስሳትን ወደ ውጭ በመላክ ንግድ መሠማራታቸውን አስታወቁ።

በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በእስያና በአውስትራሊያ የሚኖሩ የድሬደዋ ተወላጆች ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በሰጡት አስተያየት በሚሊኒየሙ በተፈጠረው መነቃቃት በከተማዋ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት አነሳስቷቸዋል።

በቶሮንቶ ካናዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፉርዶሳ ዩሱፍ በሰጡት አስተያየት፣ የሚሊኒየምና የምሥረታ በዓሉ በፈጠረው አጋጣሚ እሳቸውና በውጭ የሚኖሩ ሌሎችም ኢትዮጵያውያን በትውልድ ከተማቸው በልማትና በኢንቨስትመንት ተግባር ለመሰማራት ተዘጋጅተዋል።

በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ነዋሪ የሆኑትና ከ13 ዓመት ቆይታ በኋላ ከነቤተሰባቸው ወደ ድሬዳዋ የመጡት ወይዘሮ ሙሉመቤት በበኩላቸው፣ በውጭ ሀገር በነርስነት ሙያ በማገልግል ላይ መሆናቸውን ጠቁመው በጤናው ዘርፍ በሙያቸውና በእውቀታቸው ለማገልገልና ለከተማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

እንዲሁም በውጭ ሀገር ለሚኖሩ፣ ትውልድ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎችን ስለ ድሬዳዋና ስለኢትዮጵያ መልካም ገፅታ በማስተዋወቅ ወደ ሀገሪቱ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉና በህክምናው ዘርፍ የሚያገልግሉ ቁሳቁሶችን ይዘው በመምጣት በስጦታ መልክ ለማበርከት ማቀዳቸውንና በክረምት ለዕረፍት በሚመጡበት ወቅት ነጻ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከስዊዘርላንድ ሎዛን ከተማ የመጡት አቶ ቅዱስ አማን አየለና ከቶሮንቶ ካናዳ የመጡት ኪሚያ ናሆም የተባሉ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ከህዝብ ጋር በመሆን የድሬዳዋን ራዕይ በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፣ በከተማዋ ልማት የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በካናዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሙኒር መሀመድ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው በሚሊኒየሙ በድሬዳዋ ኢንቨስት ለማድረግ መምጣታቸውንና ፈቃድ ወስድው ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በከተማዋ ለኢንቨስትመንት በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የቀንድ ከብቶችን ወደ ውጭ በመላክና የዶሮ መፈልፈያ ማሽኖችን በማስገባት፣ በእንስሳት ማድለብ በመሳሰሉት የግብርና ዘርፎች ለመሰማራት በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

እስከ አሁን ለ25 ቋሚ ሠራተኞችና ለበርካታ ወገኖች የሥራ ዕድል በመፍጠር ራሳቸውን፣ ዜጎችንና ሀገራቸውን ተጠቃሚ በማድረግ የድርሻቸውን በማበርከት ላይ መሆናቸውን አቶ ሙኒር ጠቁመዋል።

የእሳቸውን አርአያነት በመከተል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የድሬዳዋ ወዳጆች ወደሀገራቸው ተመልስው ሀገራቸውን በማገልገል ራሳቸውም እንዲጠቀሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።