|
በከተሞች በ1 ነጥብ3 ቢሊዮን ብር ወጭ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው |
አዲስ አበባ ጥር 19/2000/ አዲስ አበባና ድሬደዋ አስተዳደሮችን ጨምሮ በሰባት ክልሎች በከተሞች አካባቢ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል በ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጭ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እያሄካደ መሆኑን የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስትሩ በየክልሎቹ እየተካሄደ ያለውን የቤቶች ልማት ፕሮግራም የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ለመገምገም ዛሬ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ባቀረበው ሪፖርት እንዳስታወቀው፤ በግማሽ ዓመት ውስጥ የግንባታ ስራቸውን ለመጀመር ከታቀዱት 2ሺ 855 የጋራ መኖሪያ ህንፃዎች መካከል የ2ሺ 290 ህንፃዎች ግንባታቸው ተጀምሯል። በቤቶቹ ግንባታ ሂደት ለ92ሺ 365 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መቻሉንና በቀጣይ ወራት የተሟላ ድጋፍ በመስጠት የሚፈጠረውን የሥራ ዕድል ማስፋት እንደሚቻል የሚኒስቴሩ የግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት አመልክቷል። የስራ ተቋራጮች ተሳትፎን በተመለከተም በበጀት ዓመቱ 744 አዳዲስ የስራ ተቋራጮች በቤቶች ልማት ፕሮግራም እየተሳተፉ ሲሆን፤ ይህም በዘርፉ የተሰማሩትን የስራ ተቋራጮችን ቁጥር ወደ 1ሺ 689 ከፍ እንደሚያደርገው ገጿል። ይሁንና በበጀት ዓመቱ ከሚያስፈልጉት 1ሺ 585 የስራ ተቋራጮች አንጻር ሲታይ ከፍተኛ የስራ ተቋራጮች እጥረት እንዳለ አመልክቶ፤ በቀጣይ ብዛት ያላቸውን የሥራ ተቋራጮችን በቤት ልማት ፕሮግራሙ ለማሳተፍ የሚያስችል የተቋራጮችና የግንባታ ዕቃዎች አቅርቦት አቅም ግንባታ ፕሮግራም ተነድፎ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል። የስራና ከተማ ልማት ሚኒስትር ዶክተር ካሱ ይላላ በዚሁ ወቅት እንዳስታወቁት፤ መንግስት በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ከተሞች እየታየ ያለውን የመኖሪያ ቤቶች ችግር ለመቅረፍ የነደፈውን ፕሮግራም ስኬታማ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በተለይም በየክልሎቹ የሚታየውን የመኖሪያ ቤቶች እጥረት ችግር አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀው።
በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን የግንባታ እቃዎች አቅርቦት ችግር ለማቃለል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከውጭ አገር ለማስገባት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ የግምገማ መድረክ ላይ ክልሎች የየራሳቸውን የግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት በማቅረብ ውይይት የሚካሄድባቸው መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|