ድርጅቶቹ ለምርጫው ከ55ሺ በላይ ዕጩዎች ማቅረባቸውን ገለጹ

አክሱም ጥር 19/2000/ዋኢማ/ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን በመጪው ሚያዚያ ወር በሚካሄደው የአካባቢና ማሟያ ምርጫ ህወሐትን ወክለው የሚወዳደሩ 49ሺ 516 ዕጩ ተወዳዳሪዎች በሕዝብ መገምገማቸውን የዞኑ የህዝብ አደረጃጀት ኃላፊ ገለጹ። የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ ለባህር ዳር ከተማ ያዘጋጃቸውን 6ሺ ዕጩዎች በህዝብ እያስገመገመ ነው።

ኃላፊው አቶ መስፍን ገብረስላሴ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በዞኑ 13 ወረዳዎች በሚካሄደው የወረዳ፣ የቀበሌና የማሟያ ምርጫ ለመወዳደር ህወሓት 24ሺ 274 ሴቶች የሚገኙባቸው 49ሺ 516 ተወዳዳሪዎችን በዕጩነት አቅርቦ በህዝብ አስገምግሟል።

በህወሓት የቀረቡ ዕጩ ተወዳዳሪዎች በየደረጃው በሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መገምገማቸውንና አስተያየት እንዲሰጥባቸው መደረጉን የገለጹት አቶ መስፍን፤ በህዝብ ተቀባይነት ያላቸው፣ መልካም አስተዳደርና ልማትን ለማስፈን የሚታገሉና የህዝብ ወገናዊነታቸውን የሚያስቀድሙ ዕጩዎች እንደሆኑ በግምገማው መረጋገጡን ተናግረዋል።

ህዝቡ ያላመነባቸው 37 ተወዳዳሪዎችም በህዝቡ ተቃውሞ ከውድድሩ እንዲገለሉ መደረጉንና በተገለሉ ተወዳዳሪዎች ምትክ በህዝቡ ምርጫ ሌሎች እንዲተኩ መደረጉን ኃለፊው ገልፀዋል።

ህወሓት ሴቶችን ወደ አመራር ለማምጣትና የሴቶች ተሳትፎን ለማሳደግ ትኩረት መስጠቱን የገለጹት አቶ መስፍን፤ በምርጫው ድርጅቱን በመወከል ለወረዳ ከሚወዳደሩ 2 ሺ 879 ዕጩዎች 51 በመቶ ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ፤ ለቀበሌ ከሚወዳደሩ 46ሺ 637 ዕጩዎች መካከልም 48 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በመጭው ሚያዚያ ወር ለሚካሄደው የአካባቢና ማሟያ ምርጫ ሁለት እጩዎችን ለህዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤት፣ 120 እጩዎችን ለከተማ አስተዳደር እንዲሁም ከ5ሺ 900 በላይ እጩዎችን ለቀበሌ አስተዳደር አዘጋጅቶ በህዝብ እያስገመገመ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአስተዳደሩ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በርሄ እንዳስታወቁት፤ በሁሉም ደረጃ የተዘጋጁት እጩዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው፣ በተሰማሩበት የስራ መስክ ግንባር ቀደም የሆኑ፣ ከደባል ሱስ ነፃ የሆኑና በመልካም ስነ ምግባራቸው በህዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ከዕጩዎቹ መካከል 30 በመቶ ሴቶችና ከ20 እስከ 30 በመቶ ወጣቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሙህራንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካተታቸውን ኃላፊው ገልፀዋል።