አዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት በእስር ላይ ለሚገኙ ኤርትራውያን የመከራ ዓመት እንደሆነባቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ታህሳስ 29/2000/ዋኢማ/አዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት በሻዕቢያ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለተፈፀመባቸውና በእስር ላይ ለሚገኙ ኤርትራውያን የመከራ ዓመት እንደሆነባቸው ተገለጸ።

"አዋቴ" የተባለውን ድረ-ገፅ ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደዘገበው፤የኤርትራ መንግስት በሚከተለው የፖለቲካና የኃይማኖት ፖሊሲ ተቃራኒ አመለካከት አላቸው በሚል በአገሪቱ ወታደራዊ እስር ቤቶች ታስረው በሚገኙ ኤርትራውያን ላይ እየፈፀመ ያለው ኢሰብዓዊ ድርጊትና የማሰቃየት ተግባር እየተባባሰ መጥቷል።

ድረ-ገጹ ባሰፈረው ዘገባ እንዳመለከተው፤ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አዲሱን ዓመት በማስመልከት ባደረጉት ንግግር የኤርትራ መንግስት በተለያዩ ምክንያቶች ያሰራቸውን በሺዎች የሚቆጠሩትን ኤርትራውያን እንዲፈታ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያቀረበውን ጥያቄ ማጣጣላቸው መንግስታቸው በእስረኞቹ ላይ የሚፈጽማቸውን ኢ-ስብኣዊ ድርጊት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚያረጋግጡ ናቸው።

በኤርትራ በርካቶች በፖለቲካ አመለካከታቸውና በዕምነታቸው ምክንያት ከአምስት እስከ 25 ዓመታት የሚደርስ እስር ተበይኖባቸው እንደሚገኙ ያጋለጠው የዜና ምንጩ፤ ከነዚህም መካከል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያክ አቡነ አንቶንዮስን ጨምሮ በርካታ የሌሎች የክርስትናና የእስልምና ኃይማኖት መሪዎች እንደሚገኙባቸው ጠቁመዋል።

እስረኞቹ በጨለማ ቤቶችና ብረት ኮንትቴነሮች ታጉረው ለከፍተኛ ሙቀትና ቅዝቃዜ ስለሚዳረጉ የብዙዎቹ ህይወት እንደሚያልፍ ያመለከተው ድረ-ገፁ ፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የሰብኣዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት በኤርትራ እስር ቤቶች ታስረው በሚገኙ እስረኞች ላይ አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ የተለያየ ስቃይ እየተፈፀመባቸው እንደሆነ ማረጋገጡን ዘገባው አብራርቷል።

የሻዕቢያ የፀጥታ ኃይሎች የተለያዩ የማሰቃያ ስልቶችን በመጠቀም እስረኞች የፖለቲካ አመለካከታቸውን እንዲለውጡና ሐይማኖታቸውን እንዲክዱ ማስገደድ መቀጠላቸውን ድረ-ገፁን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርማሽን ማዕከል ዘግቧል።