የአፍሪካ አገራት የወጣቶችን ጉዳይ እንደ አንድ አጀንዳ ይዘው መወያየት መቻላቸው ለወጣቱ የሰጡትን ትኩረት ያሳያል ተባለ

አዲስ አበባ ጥር 6/2000/ዋኢማ/ የአፍሪካ አገራት የወጣቶችን ጉዳይ እንደ አንድ አጀንዳ ይዘው መወያየት መቻላቸው የአፍሪካ መንግስታት ለጉዳዩ የሰጡትን ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሳይ በስብሰባው ላይ ተካፋይ የሆኑ የተለያዩ አገራት ተወካዮች ገለጹ።

በወጣቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚነጋገረው የአፍሪካ ህብረት ሚኒስትሮች ቋሚ ኮሚቴ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተሳታፊ ከሆኑት የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተወካዮች መካከል አንዳንዶቹ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዛሬ አንደገለጹት፣ የአፍሪካ ወጣቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ አተኩረው መሳተፍ መቻላቸው ለአህጉሪቱ እድገትና ብልጽግና የጎላ አስተዋጽኦ አለው።

ከናሚቢያ የመጣውና የወጣቶች ተወካይ የሆነው ማንዴላ ካፔሬ እንደገለጸው፣ የአፍሪካ ህብረት የወጣቶች ቻርተር በአፍሪካ መሪዎች ባለፈው ዓመት መጽደቁንና ህብረቱ አጀንዳው ላይ ይዞ በጉዳዩ ላይ መወያየቱ በአፍሪካ ወጣቶች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ሁለንተናዊ ተሳተፎ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል።

ወጣት ማንዴላ ካፔሬ

የአፍሪካ ወጣቶች ቻርተር ተግባራዊ ሲሆን የአህጉሪቱን ወጣቶች በትምህርት፣ በስራ ፈጠራ፣ በጤናው ዘርፍ በተለይም በኤች አይ ቪ ኤድስና በሌሎችም ተጓዳኝ ተግባራት ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማስቻል ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ገልጸዋል።

በናይጄሪያ የሴቶች ሌደርሺፕ ፎረምን ወክላ የተገኘችው ሉሲያ ኦኚዋዱሜ በበኩሏ፣ የያዝነው አዲሱ የፈረንጆች ዓመት "የአፍሪካ የወጣቶች ዓመት" ተብሎ መወሰኑ በአህጉሪቱ አብዛኛውን የቁጥር ድርሻ ያላቸው ወጣቶች ለአህጉሪቱ እድገትና ብልጽግና የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ በመረዳት መሆኑን ገልጻለች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአፍሪካ አገራት ለወጣቶች ተገቢውን ትኩረት በመስጠቱ ረገድ ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ጠቁማ፣ ወጣቶችም በአገራቸው የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ዘርፎች ለመሳተፍና ውጤት ያለው ተግባር ለማከናወን ብቃት ያላቸው መሆኑንም አመልክታለች።

ወጣት ሉሲያ ኦኚዋዱሜ

የአፍሪካ ወጣቶች ቻርተር ተግባራዊ እንዲሆን 16 አገራት ወስነው የፈረሙ ሲሆን፣ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህ ቻርተር ሌሎችም አገራት በአፋጣኝ ፈርመው ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ሉሲያ ኦኚዋዱሜ አመልክታለች።

የአፍሪካ ታዳጊዎችና ወጣቶች በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዳሉባቸው የገለጹት በሴኔጋል የወጣቶችና የስራ ሚኒስቴር ተወካይ ሚስተር ሲሬ ሎ፣ ወጣቶቹ ካሉባቸው መሰረታዊ ችግሮች ነጻ እንዲሆኑ ለማስቻል በሚደረገው ጥረት በተለያዩ ማህበራት መደራጀታቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ወጣቶች ቻርተር ጸድቆ ተግባራዊ ሲሆን የአህጉሪቱን ወጣቶች መሰረታዊ ችግሮች ለማቃለል አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመው፣ በዚህም ረገድ የአፍሪካ መንግስት የስራ ሀላፊዎች ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።