ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሚያዚያ አምስት በተካሄደ ምርጫ ያሸነፉ ዕጩዎችን ጊዜያዊ ውጤት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ ሚያዚያ15/2000/ዋኢማ/ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፅህፈት ቤት ሚያዚያ 5/2000 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማሟያና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ምርጫ ያሸነፉ ዕጩዎችን ጊዜያዊ ውጤት ይፋ አደረገ።

የፅህፈት ቤቱ ዋና ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መንገሻ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ሚያዚያ አምስት በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደውን የከተማ አስተዳደር ምክር ቤትና ማሟያ ምርጫ ውጤት በተሻሻለው የምርጫ ህግ መሰረት በተሰጠው ስልጣን ከምርጫ ክልሎች የተሰበሰቡትን ጊዜያዊ ውጤት ይፋ አድርጓል።                                                                  አቶ ተስፋዬ መንገሻ

በመቀጠልም ከሌሎች የምርጫ ክልሎች የሚሰበሰቡትን የምርጫ ውጤቶች በተከታታይ ይፋ እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ አጠቃላይ የምርጫው ውጤት በመጪው ግንቦት 10/2000 ዓ.ም. እንደሚገለጽ ገልጸዋል።

ዛሬ በጽህፈት ቤቱ በተለጠፈው ጊዜያዊ ውጤት መሰረት ከአዲስ አበባ በተካሄዱ 14 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሟያ ምርጫ ሁሉንም ኢህአዴግ ያሸነፈ ሲሆን፤ ለዚህ ምርጫ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢህአዴግ፣ ቅንጅት፣ ኦፍዴን፣ ኦብኮ፣ ኢዴአፓ መድህን፣ መኢብን፣ ኢዴህ፣ ኦነብፓና የግል ተወዳዳሪዎች መወዳደራቸውን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተካሄደው የከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ምርጫ ከተወዳደሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በ10 ክፍለ ከተሞች ኢህአዴግ ያሸነፈ ሲሆን፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ አንድ ወንበር ቅንጅት ማሸነፉን ገልፀዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በ39 ምርጫ ክልሎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሟያ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ 14 ሌሎች 25 ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መካሄዱን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።