|
ዩኒቨርስቲው በመጪው ዓመት አዳዲስ የዶክርትሬትና የማስተርስ ዲግሪ መርሃግብሮችን ሊከፍት ነው |
አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/1999/ዋኢማ/ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጪው የትምህርት ዘመን የዶክትሬትና የማስተርስ ዲግሪ ስልጠና ፕሮግራሞችን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ የምርምርና የትምህርት ማዕከላትን ለመክፈት የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን አስታወቀ። በዩኒቨርስቲው የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተባባሪ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የሪፎርምና የስትራቴጂክ ዕቅድ ዳይሬክተር ዶክተር አብይ ጣሴ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ በመጪው ጥቅምት ወር የሚጀመሩት አዳዲስ የዶክትሬትና የማስተርስ ዲግሪ ስልጠና ፕሮግራሞችና የምርምር ስራዎች የዩኒቨርስቲውን የቀጣይ አምስት አመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መነሻ በማድረግ የተዘጋጁ ናቸው። በዶክትሬት ዲግሪ ስልጠና ከሚሰጥባቸው የትምህርት መስኮች መካከል የአካባቢ ልማት፣ የምርምር ልማት ማህበራዊና ስነ ጾታ ትምህርት መስኮች ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልፀዋል። እነዚህም በዩኒቨርስቲው ሥር በሚቋቋም የልማት ጥናትና ምርምር ኮሌጅ አማካኝነት የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በህክምና ዘርፍ ያሉት የፋርማሲ፣ የእንስሳት ህክምናና ሌሎችም የትምህርት ዘርፎችን በማሰባሰብ ራሱን የቻለ አንድ የስልጠናና የምርምር ተቋም እንደሚደራጅ ዶክተር አብይ አመልክተው የንግድ ስራ ኮሌጅና የፋይናንስ ጥናት አካዳሚ የማዋሃድ ተግባርም እንደሚከናን አስረድተዋል። በውሃ ቴክኖሎጂ፣ በማህበረሰብ ሳይንስ፣ በኢንፎርማቲክስ፣ በምግብዋስትናና በሌሎች ተያያዥ ዘርፎች ላይ የማስተርስ የስልጠና ፕሮግራም የሚጀመረው ሲሆን በተጓዳኝም በርካታ የምርምር ስራዎች እንደሚካሄዱ አመልክተዋል። ከዚህም ሌላ ዩኒቨርስቲው ከሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር የሰላምና ደህንነት፣ በፌዴራሊዝምና ፓርላመንታዊ ስርዓት ዙሪያ የማስተርስ ትምህር ለመስጠት አዳዲስ ኢንስቲትዩቶች መቋቋማቸውንና ተቋማቱ የጥናትና ምርምር ስራ ለማካሄድ አጋዥ መሆናቸውን አስታውቀዋል። /ለኢቴቪ የዶክተር አብይን ድምፅ ተጠቀሙ/ "አዳዲስ ኢንስቲትዩሽኖች የተከፈቱ አሉ ወደፊትም ይከፈታሉ ለምሳሌ በሰላምና የደህንነት ተቋም ተቋቁሟል። እናም አንገብጋቢ የሚባሉ ተቋማትን በመክፈት ላይ ነው ያለነው እንግዲህ ይህ ከአገሪቷ እድገት ጋር አብሮ ተጣጥሞ የሚሄድ ነው በሚል ነው ።" ተቋማቱ የመንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለማስፈፀም የሚያግዝ የሰው ኃይል ለማፍራትና ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ለማካሄድ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ ዶክተር አብይ አስረድተዋል። ዩኒቨርስቲው በቀጣይም ሌሎች አዳዲስ የስልጠናና የምርምር መስኮችን ለመክፈት ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልፀው፤ ይህም በቀጣዮቹ ጥቂት አመታት በአገሪቱ ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያለባቸውን የሠው ኃይል እጥረት እንደሚያቃልል አብራርተዋል። ዩኒቨርሲቲው በተያዘው የትምህርት ዘመን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂና በኢንጅነሪንግ የትምህርት ክፍል 40 ሰልጣኞችን በዶክትሬት ዲግሪ መርሃግብር ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ ዶክተር አብይ ተናግረዋል። ዩኒቨርስቲው ባስቀመጠው የቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድ መሠረት በማስተርስና በዶክትሬት ዲግሪ በተለያዩ የትምህርት መስኮች አዳዲስ ፕሮግራሞችን መክፈቱን እንደሚቀጥል ዶክተር አብይ መግለጻቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|