|
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተወሰኑ ጋዜጠኞች እንዲከላከሉ ወሰነ |
| አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/1999 ሕገመንግሥቱንና በሕገመንግሥቱ መሠረት የተቋቋመውን ሥርዓት በአመጽ ለማፍረስ በፈጸሙት የሙከራ ወንጀል ክስ በተመሠረተባቸው በእነ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል መዝገብ ከተከሰሱት የህትመት፣ የማስታወቂያ ድርጅቶችና የጋዜጣ አዘጋጆች መካከል የተወሰኑት እንዲከላከሉ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት ብይን ሰጠ፡፡ በአምስተኛው ክስ ደግሞ ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ የጦርነት ስጋት እየፈጠረች በነበረችበት ጊዜ የቅንጅት መሪዎች በሚያካሂዷቸው ውይይቶችና ይሰጧቸው በነበሩ መግለጫዎች መነሻነት ሕገወጥ አላማቸውን ለማሳካት የሀገር መከላከያ ንብረት የሆነ መኪና በማቃጠልና በመጉዳት ቅንጅቱን ይመሩ ከነበሩት 16 ተከሳሾች መካከል ኢንጂነር ኃይሉ ሻውልን ጨምሮ አስሩ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ሲሳይ የህትመትና የማስታወቂያ ድርጅት፣ ዘካሪያስ አሳታሚ፣ ሰርካለም አሳታሚ ድርጅት፣ የኢትኦጵ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ አንዱዓለም አየለ፣ የአባይ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ መስፍን ተስፋዬ እና የሳተናው ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ዳዊት ፋሲል እንዲከላከሉ ብይን ሲሰጥ ጉዳያቸው በሌሉበት የታየው የምኒልክ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ዘላለም ገብሬ እና የነፃነት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ አብይ ግዛው ላይ ደግሞ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በሁለተኛው ክስ በቅንጅት ላእላይ ምክር ቤት ይደረጉ በነበሩት ስብሰባዎች የምርጫ ቦርድ በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ስልጣን መሠረት ተግባሩን እንዳያከናውን የማሰናከል ድርጊት ፈጽመዋል ተብለው ክስ ktm\rtÆቸውÂ ጉዳያቸው ባሉበት የታየው 21 ተከሳሾች እንዲከላከሉ ጉዳዩ በሌለበት የታየው ብሩክ ከበደ ላይ ደግሞ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በሦስተኛው ክስ በቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ በተሰኘ ድርጅት ስር ተሰባስበው በሕገመንግሥቱ በተቋቋሙ አካላት ላይ የኃይል ጥቃት ለመፈፀም ሕገ ወጥ ታጣቂዎችንና ሽፍታዎችን የማደራጀት ሥራ ማከናወናቸው በማስረጃ የተረጋገጠባቸው ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል፣ አቶ ማሙሸት አማረ፣ አባይነህ ብርሃኑና ሻለቃ ጌታቸው መንግሥቴ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡ በአንደኛው ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ 25 ጋዜጠኞች፣ የሕትመትና የማስታወቂያ ድርጅቶች ኃላፊዎችና ባለቤቶች ደግሞ መከላከል አያስፈልጋቸውም በማለት ፍርድ ቤቱ ብይን በመስጠት ከማረሚያ ቤት እንዲፈቱ ዋራንት እንዲጻፍ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ እንዲሁም በሁለተኛው ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ 37 ሰዎችና ድርጅቶች ደግሞ መከላከል አያስፈልጋቸውም ሲል ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡ በአምስተኛው ክስ ደግሞ ሕገወጥ አላማቸውን ለማሳካት ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ የጦርነት ስጋት እየፈጠረች በነበረችበት ጊዜ የቅንጅት መሪዎች ከጥቅምት ወር 1997 ዓ.ም ጀምሮ በሚያካሂዷቸው ውይይቶችና ይሰጧቸው በነበሩ መግለጫዎች መነሻነት የሀገር መከላከያ ንብረት የሆነ መኪና በማቃጠልና በመጉ ዳት ቅንጅቱን ይመሩ ከነበሩት 16 ተከ ሳሾች መካከል ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል፣ አቶ አባይነህ ብርሃኑ፣ ሻለቃ ጌታቸው መንግሥቴ፣ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፣ አቶ ሙሉነህ ኢዮኤል፣ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ ዶክተር በፈቃዱ ደግፌ፣ ዶክተር ኃይሉ አርአያ፣ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያምና አቶ ስለሺ ጠና የተባሉት እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡ በአንደኛው ክስ የተመሰረተባቸው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት -መኢአድ-ቅንጅት? የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ-መድህን፣ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሊግ እና ቀስተደመና ኢትዮጵያ የዴሞክራሲና የማኅበራዊ ፍትህ ንቅናቄ (ቀስተደመና(QNJT) የፖለቲካ ድርጅት የሚከሰሱት በሌላ አንቀፅ መሆኑን በመግለፅ አሁን በክሱ የተጠቀሰባቸው የሕግ አንቀፅ የሚከሰሱበት ባለመሆኑ መከላከል አያስፈልጋቸውም ሲል ችሎቱ ብይን ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በትናንት ውሎው ዓቃቤ ሕግ በተራ ቁጥር ስድስትና በተራ ቁጥር ሰባት ያቀረባቸውን ክሶች አይቶ ተከሳሾቹ መከላከል አያስፈልጋቸውም በማለት በአብላጫ ድምጽ ብይን ሰጥቷል፡፡ በሃሳብ የተለየው አነስተኛው ድምጽ ደግሞ በአገር ክህደቱና በዘር ማጥፋት ወንጀሉ በተከሳሾች ላይ የተመሰከረባቸው በመሆኑ ሊከላከሉ ይገባል በማለት የሃሳብ ልዩነቱን አስቀምጧል፡፡ በተመሰረተባቸው ክስ መልስ ሳይሰጡ የቆዩት ተከሳሾች ተከላከሉ የተባሉበት የሕግ አንቀጽ ከባድ በመሆኑ መከላከል ይፈልጉ እንደሆነ ሃሳባቸውን አስተካክለው እንዲመጡ ወይም በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያመለክቱ ትእዛዝ በመስጠት ለሚያዝያ 22 ቀን 1999 ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ጠበቃ አቁመው ይከራከሩ የነበሩት ተከሳሾችም የመከላከያ ማስረጃ ካላቸው በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያቀርቡና መጥሪያ ወስደው የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አስቀርበው እንዲያሰሙ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ዓቅቤ ሕግ በተራ ቁጥር አራት ቀርቦ የነበረውን ክስ ቀደም ሲል ማንሳቱ ይታወሳል፡፡ ኢዜአ |
|
|
|
|