ኢትዮጵያ የምዕተ ዓመቱን ግብ ለማሳካት ባስመዘገበችው እጅግ አበረታች ውጤት በመንግስታቱ ድርጅት ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ገለጻ እንድታደርግ ተመረጠች

አዲስ አበባ ሚያዚያ 2/1999/ዋኢማ/ ኢትዮጵያ የምዕተ ዓመቱን ግብ ለማሳካት ባደረገችው ጥረት እጅግ አበረታች ውጤት በማስመዝገቧ በመጪው ሐምሌ ጀኔቫ ላይ በከፍተኛ ሚኒስትሮች ደረጃ በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ምክር ቤት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ውጤታማነቷን በተመለከተ ገለፃ እንድታደርግ መመረጧ ተገለፀ። ጋናም የዚሁ ዕድል ተጋሪ መሆኗን ተገልጿል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የምስራቅ አፍሪካ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ፓትሪክ ቡጌምቤ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ የምዕተ ዓመቱን ግቦች ለማሳካት ውጤታማ ስራ በማከናወኗ አገሪቱ ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች በተመለከተ በመንግስታቱ ድርጅት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ገለፃ እንድታደርግ ተጠይቃለች።

[የዳይሬክተሩ ድምፅ]

" ኢትዮጵያ የምዕተ ዓመቱን ግቦች ላማሳካት እጅግ አመረቂ ተግባሮችን አከናውናለች። ስለዚህም አገሪቱ ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች በተመለከተ ጄኔቫ ላይ በከፍተኛ ሚኒስትሮች ደረጃ በሚካሄደው ዓመታዊ የተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ምክር ቤት ላይ ተገኝታ ገለጻ እንድታደርግ ተጠይቃለች። እኛም አገሪቱ በስብሰባው ላይ ተግኝታ ገለጻ ለማድረግ ለምታደርገው ዝግጅት ዕገዛ እናደርጋለን።"

በዚህም ጽህፈት ቤቱ ኢትዮጵያ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አማካኝነት በስብሰባው ለመገኘት የምታደርገውን ዝግጅት በመደገፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ይህም አገሪቱ የምዕተ ዓመቱን ግቦች በማሳካት ረገድ ያስመዘገበችው ስኬት ለዓለም ህብረተሰብ ማሳየት እንደሚያስችላት አመልክተዋል።

ጋናም ባከናወነችው ውጤታማ ስራና ባስመዘገበችው አበረታች ውጤት ከኢትዮጵያ እኩል በስብሰባው ላይ ገለፃ እንድታደርግ መመረጧን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም ባንክና ሌሎች መሰል ተቋማት በኢትዮጵያ የታየውን የዋጋ ግሽበት በተመለከተ ከሚያካሂዳቸው ጥናቶች በተጨማሪ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የምስራቅ አፍሪካ ጽህፈት ቤት በዋጋ ግሽበቱ ላይ ጥናት እንዲያካሂድ የኢትዮጵያ መንግስት መጠየቁን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄውን ያቀረበው በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚታየውን የዋጋ ግሽበት በተመለከተ እንደ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ባሉ ገለልተኛ ተቋማት ቢረጋገጥ የተሻለ ነው ብሎ ስለሚያምን እንደሆነም አስረድተዋል።

የአፍሪካ አኮኖሚክ ኮሚሽን የምስራቅ አፍሪካ ክፍለ አህጉራዊ ዕህፈት ቤት ከግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ የምታካሂዳቸውን የገጠር ልማት ስራዎች ለማገዝ እንደሚሰራም ዳይሬክተሩ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።