በጎንደር ከተማ መጪውን ሚሊኒየም በታላቅ ድምቀት ለማክበር የሚያስችል ምክርቤት ተቋቋመ

ጎንደር ሚያዝያ 2/1999/ዋኢማ/በጎንደር ከተማ መጪውን ሚሊኒየም በታላቅ ድምቀት ለማክበር የሚያስችል የሀገር ሽማግሌዎችንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ ምክርቤት ተቋቋመ።

በጎንደር ከተማ ሰሞኑን በተካሄደ የሚሊኒየም መሥራች ጉባኤ የተቋቋመው ምክርቤት የከተማዋ ታዋቂ የአገር ሸማግሌዎች የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞችንና የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያቀፈ ነው።

በመሥራች ጉባኤው የተቋቋመው የሚሊኒየም ምክር ቤት በሥሩ 11 ሥራ አስፈፃሚ አባላት ያሏቸው ስድስት ንዑሳን ኮሚቴዎችአሉት።

የሚሊኒየም ምከርቤቱ አባላት ባስተላለፉት መልክት በጎንደር ከተማ ሊሰራ የታቀደውን ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ ለማስጀመር፤ኤች አይቪ ኤድስን ለመከላከል፤ከተማዋን ማስዋብ፤ቅርሶችንና የተፈጥሮ ሀብቶችን

ለመንከባከብ ኅብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል።

በሚሊኒየም ምክር ቤቱ መሥራች ጉባኤ የተገኙት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ መጋቢያው ጣሰው ባደረጉት ንግግር፤ ከተማዋ በአገሪቱ ታሪክ የነገስታት መናገሻ በመሆን ያላትን ፈርጀ ብዙ ታሪክ በማስተዋወቅ ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ የከተማዋ ነዋሪ በዓሉን ለማክበር መነሳሳት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ሚሊኒየሙን በማስመልከት በከተማዋ አንገረብ ግድብ አካባቢ ሊቋቋም ለታሰበው ፓርክ በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ጀምበርና የአማራ መልሶ መቋቋም ልማት ድርጅት /አመልድ/ዳይሬክተር አቶ ውለታው ሀይለማሪያም የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል።

የአማራ መልሶ መቋቋም ልማት ድርጅት /አመልድ/ዳይሬክተር አቶ ውለታው ኃይለማሪያም እንደተናገሩት፣ የከተማዋን የተፈጥሮ ሀብት ለመንከባከብ ለሚደረገው ጥረት አመልድ ከ3 ሚሊየን በላይ ልዩ ልዩ ችግኞችን ለማቅረብ ቃል ገብተዋል።

በመሥራች የሚሊኒየም ምክር ቤቱ ጉባኤ በከተማዋ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብለው የታመነባቸው ከሚሊኒየሙ ጋር ተያይዘው ሊሰሩ የታቀዱ ዝርዝር ፕሮጀክቶች ቀርበው መጽደቃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።