|
ሻዕቢያ በኩናማ ብሄረሰብ አባላት ላይ የሚያደርገውን አፈና አጠናክሮ መቀጠሉን ተገለጸ |
መቀሌ ሚያዝያ 2/1999/ዋኢማ/ የሻዕቢያ መንግስት በኤርትራውያን ላይ በተለይም በጋሽ ባርካ አካባቢ በሚገኙ የኩናማ ብሄረሰብ አባላት ላይ የሚያደርገውን አፈና አጠናክሮ መቀጠሉን የኤርትራ ኩናማ ዴሞክራሲያዊ ነጻነት እንቅስቃሴ/ደምሐኩኤ/ ገለጸ። የኤርትራ ኩናማ ዴሞክራሲያዊ ነጻነት እንቅስቃሴ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጸው፤ የሻዕቢያ መንግሥት ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማት በሚወስዳቸው ኤርትራውያን ተቃውሞ እየበረታበት ባለበት በአሁኑ ወቅት በተለይም ካለፈው ወር ጀምሮ በኩናማ ብሄረሰብ አበላት ላይ መጠነ ሰፊ አፈና እያካሄደ ይገኛል። የሻዕቢያ መንግሥት እየተከተለ ባለው የአፈና ስልት አፋኝ አባላቱን በተራሮች፣ በኮረብታዎችና በየጢሻው በማሰማራት ለእርሻ ስራ የተሰማሩ የኩናማ ወጣቶችን አስገድዶ መውሰድ ሲሆን፤ ወጣቶቹ እንዳያመልጡ አሊያም ተቃውሞአቸውን እንዳያሰሙ ጫማቸውን አስወልቆ እጃቸውን በገመድ አስሮ ረጅም መንገድ እንዲጓዙ በማድረግ እንያሰቃያቸው እንደሚገኝ አመልክተዋል። እንዲህም ሆኖ ለማምለጥ የሚሞክሩትን ያለምንም ርህራሄ በጥይት እንዲገደሉ በማዘዝ በየሜዳው ወድቀው እንዲቀሩ እያደረገ መሆኑን ድርጅቱ አጋልጧል። ሻዕቢያ በእጁ የወደቁት ኤርትራውያንን በሞቃታማነቱ ወደ ታወቀው ዊዓ ማሰልጠኛ ማዕከል እንደሚወስዳቸውና በኪሳቸው የተገኘ ገንዘብና ንብረትም እንደሚቀማቸው ድርጅቱ አመልክቷል። ሻዕቢያ ወደ ዊዓ ከወሰዳቸው በርካታ የኩናማና የሌሎች ብሄር ተወላጆች በተለይም ታዳጊ ወጣቶች ሙቀቱን መቋቋም አቅቷቸው ለከባድ የሥነ ልቦና ጭንቀት በመጋለጣቸው ወደ ሳዋ ማሳልጠኛ ተቋም እያዛወራቸው እንደሚገኝም አስታውቋል። አፋኙ የሻዕቢያ ወታደራዊ ኃይል በኩናማ ሚሊሻዎች ተቋውሞ መደናገጡን ድርጅቱ ጠቅሶ፤ የኩናማ ሚሊሻዎች በአካባቢያቸው ወደ ሚገኘው ከርካሻና በረንቱ መስተዳድሮች መሳሪያዎቻቸውን እንዲያስረክቡ እያደረገ መሆኑንም ገልጿል። የሻዕቢያ መንግሥት ተስፋ እየቆረጠ በመምጣቱ በቅርቡ በበረንቱ ከተማ ባደረገው ስብሰባ የኤርትራ ነጻነት የመጣው የሚያጠቡ እናቶች ጭምር ባደረጉት ተጋድሎ ስለሆነ ከሁለት እስከ ሦስት የወለዱ እናቶች መሳሪያ እንዲታጠቁ አዲስ መመሪያ ማውጣቱን ድርጅቱ ገልጿል። በስብሰባው የተገኙ እናቶችም በሻዕቢያ መንግሥት የወጣውን መመሪያ መቃወማቸውንና በግዳጅ ያዘመተናል የሚል ሥጋት ላይ መውደቃቸውን ድርጅቱ አመልክቷል። |
|
|
|
|