ጉባኤው በአፈጻጸምና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ በሚታዩ ችግሮች አወጋገድ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚወያይ ተገለጸ

መቀሌ ነሐሴ 29/1998/ዋኢማ/ በመጪው መስከረም በመቀሌ ከተማ የሚካሄደው 8ኛው የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ በልዩ ልዩ ዕቅዶች ላይ የሚታዩ የአፈጻጸም ብቃት ማነስ ችግሮችንና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችን ለማስወገድ የሚያስችሉ ውሳኔዎች ተወያይቶ ያስተላልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የህወሐት/ኢህአዴግ ሊቀ መንበር አቶ መለስ ዜናዊ ገለጹ። በመሪነት ደረጃም ወጣቱ ትውልድ ነባሩን እየተካ የሚሄድበት አሰራር ሊመቻች እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

አቶ መለስ ዜናዊ ስምንተኛው የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤን አስመልክተው ትናንት ከድምፅ ወያነ ትግራይ ሬድዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ ጉባኤው የድርጅቱ መሠረታዊ ዓላማዎች ማስፈጸሚያ ምሰሶዎች በሆኑ የአፈጻጸም ብቃትና መልካም አስተዳደር ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችና ጉድለቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይነጋገራል።

መልካም አስተዳደርንና የአፈጻጸም ዓቅምን በማጎልበት በኩል በክልሉም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች አበረታች ውጤቶች ቢኖሩም ከህዝብና ከድርጅቱ ፍላጎት አንጻር ሲታዩ ገና ሊወገዱ የሚገባቸው በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ጉባኤው ህዝቡና ድርጅቱ ባልረካባቸው በመልካም አስተዳደርና በዕቅዶች አፈጻጸም ብቃት ዙሪያ ያሉትን ችግሮች ለማስወገድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በጥልቀት በመወያየት የመፍትሄ ሐሳቦችና ውሳኔዎች ያሰተላልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል።

ጉባኤው በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚነጋገረው ለድርጅቱ መሠረታዊ ዓላማዎች መሰካትና አለመሳካት ካላቸው ወሳኝ ሚና አንጻር በመሆኑ እንደሆነም አቶ መለስ አስረድተዋል።

በመሪነት ደረጃም ወጣቱ ትውልድ ነባሩን እየተካ የሚሄድበት አሰራር ሊመቻች ይገበዋል ያሉት አቶ መለስ፤ ይህንን ለማረጋገጥ ሁሉም በአመራር ላይ የሚገኘው አካልና አባሉ ለተግባራዊነቱ በቂ ዝግጅትና ትግል ማድረግ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎች ድርጅቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋገሩ እንደሚሆኑ የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ የትግራይ ህዝብ ብሎም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠብቃቸውን ፈጣን የሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማት ለውጦችን ይበልጥ ለማረጋገጥ ሁሉም ሊረባረብ እንዳለበት አመልክተዋል።

ባሁኑ ወቅት በአገራችን እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን ለውጥ ለማሰናከል የሻዕቢያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ አዲስ የሽብር ስትራቴጂ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን አቶ መለስ ገልጸዋል።

የሻዕቢያ መንግሥት ፊት ለፊት መግጠምን ትቶ የሱማሊያና ሌሎች አሸባሪ ቡድኖችን በማስታጠቅ፣ በመደገፍና በማሰማራት የኢትዮጵያ መንግሥትን ለማዳከም አልያም ለማፍረስ የሚከተለው የጦርነት ስትራቴጂና የጥፋት ተልዕኮ ሊሳካለት እንደማይችል አስገንዝበዋል ።

ቂምና አውዳሚ አስተሳሰብ የተጠናወተው የሻዕቢያ መንግሥት ባሁኑ ሰዓት ለሰላም ዝግጁነት የለውም ያሉት አቶ መለስ፤ እየተከተለ ያለው አዲስ የሽብር ስትራቴጂ እንደማይሰራ ከጊዜ በኋላ ሲያረጋግጥ ወደ ሰላም መንገድ ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ማለታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።