ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ30 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባ ሁለ ገብ ህንፃ ተጠናቆ ርክክብ ተካሄደ

አዲስ አበባ ጥቅምት 9/1999/ዋኢማ/ ትምህርት ሚኒስቴር ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ30 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባው ሁለ ገብ ህንፃ ተጠናቆ ርክክብ ተካሄደ። ህንጻው ዩኒቨርስቲው እያካሄደ ላለው የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ማስፋፊያ እንደሚያግዝ ተገልጿል።

በአራት ኪሎ ካምፓስ ውስጥ የተገነባው ህንጻ ዛሬ ደኤምሲ ኮንስትራክሽን በተባለ ተቋራጭና በትምህርት ሚኒስቴር መካከል በተደረገው የርክክብ ስነ-ስርዓት ላይ እንደተገለጸው፤ ዩኒቨርስቲዎች ሀገራዊ የልማት ፖሊስዎችንና ስትራቴጂዎችን ለማስፈጸም የሚችል ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት እንዲችሉ በመካሄድ ላይ ባለው የዓቅም ግንባታ መሰረት የተገነባው ይኸው ህንፃው ለድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ማካሄጃ ይውላል።

የሳይንስ ፋካሊት ዲን ዶክተር አርአያ አስፋው በስነ-ስርዓቱ ላይ እንድተናገሩት፤ ፋካሊቲው በቅድመ ምረቃ ፕሮግራም ብዛት ያላቸው ተማሪዎች በማስተናገድ ላይ በመሆኑ የክፍል ጥበት ገጥሞት እንደነበር ገልጸው፤ የህንፃው መገንባት ችግሩን እንደሚያቃልልና የድህረ-ምረቃ ፕሮግራምችን በሙሉ በአንድ ህንፃ ለማካሄድ ያስችላል ብለዋል።

የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ ሙከራዎችና ቢሮዎችን በአንድ ላይ አካቶ የያዘና ምድር ቤትን ጨምሮ ዘጠኝ ፎቆች ያሉት ይኸው ዘመናዊ ህንፃ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሳይንስ ዘርፍ በተያዘው ዓመት ለመጀመር ዝግጅት ባጠናቀቀባቸው አምስት አዳዲስ የድህረ - ምረቃ ፕሮግራሞችን ጨምሮ ሌሎች ነባር ፕሮግራሞችን ለሚከታተሉ ከአንድ ሺ በላይ ተማሪዎች አገልግሎት እንዲሚሰጥ ዲኑ ተናግረዋል።

ዛሬ ርክክብ የተደረገበት ይኸው ህንጻ የትምህርት ሚኒስቴር በነባር ዩኒቨርስቲዎች እያካሄደ ያለው የማስፋፊያ ግንባታ አካል እንደሆነም በርክክብ ስነ ስርዓቱ ወቅት ከተደረገው ገለጻ መረዳት መቻሉን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።