ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓመቱ የትኩረት አቅጣጫ የፓርላማ አባላት ላነሱዋቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጡ

ጥቅምት 9/1999/ዋኢማ/ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በፌደራል ምክር ቤቶች መክፈቻ ባቀረቡት የቀጣይ ዓመት የትኩረት አቅጣጫ ላይ በመንተራስ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማብራሪያ ሰጡ።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ መስከረም 29/1999 ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ በጠቆሙት የመንግስት የዓመቱ የትኩረት አቅጣጫ በመንተራስ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ላነሱዋቸው ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስሚንቶ ዋጋ መጨመርን አስመልክቶ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በስሚንቶ የዋጋ መጨመርና እጥረት ምክንያት በርካታ የግንባታ ሥራዎች መቆማቸውን ጠቁመው፤ ችግሩን ለመፍታት የግል ባለሀብቶች ስሚንቶ በማምረት ትርፋማ ለመሆን የሚያስችላቸውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ባለሀብቶቹ ከ10 የማያንሱ የስሚንቶ ፋብሪካዎችን እንደሚያቋቁሙና ግንባታቸው በሶስት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው፤ የግል ባለሀብቶችና ኮንትራክተሮች ስሚንቶ ከውጭ እንዲያመጡ በስሚንቶ ላይ ተጥሎ የነበረው የጉምሩክ ክፍያ መነሳቱን አስረድተዋል፡፡

በሚቀጥሉት ዓመታት በርካታ ስሚንቶ አገር ውስጥ ስለሚገባ አሁን ካለበት ዋጋ እንደሚቀንስና የተስተጓጐለውን የግንባታ ሂደት እንደሚያቃልለውም ገልፀዋል።

የስኳር ዋጋ ፍጆታ በተለይ በገጠር አካባቢ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ መንግስት የተለያዩ ማስተካከያዎችን ማድሩጉን የገለፁት አቶ መለስ ፤ያለተጨማሪ እሴት ታክስና የጉምሩክ ቀረጥ ስኳር ከውጭ እንዲገባ በመደረጉ የዋጋ መረጋጋት መታየቱን ተናግረዋል።

የምግብ ሰብሎች ዋጋ የጨመረው አርሶ አደሩ ገበያ ተኮርና በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን አምርቶ ወደ ውጭ በመላክ ተጠቃሚ በመሆኑና ነጋዴዎችና አከፋፋዮች የተፈጠረውን የእህል ዕጥረት በማባባስ በከፍተኛ ዋጋ በመሸጣቸው ነው ብለዋል፡፡

ችግሩን ለማስወገድም የምግብ ሰብሎች ወደ ውጭ እንዳይላኩ መከልከሉን ጠቅሰው፤ የምግብ ሰብል ምርት እንዲጨምር ማድረግ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ አንዳንድ ነጋዴዎችና አከፋፋዮች እያከናወኑ ያሉትን ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማስቀረት ጥናት እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት አስመልክተው ከሶማሌ የሽግግር መንግስትና ከሶማሌ ህዝብ ጋር ያለው ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ጠቁመው፤ በእስልምና ፍርድ ቤቶች ዙሪያ የተሰባሰቡ ጅሐዲስቶች በኢትዮጵያ የጅሀድ ጦርነት በማወጃቸው የሻከረ ግንኙነት መኖሩን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰራዊት በኢጋድና በአፍሪካ ህብረትና ዕቅድና እውቅና መሰረት ለሶማሌ የሽግግር መንግስት የፖሊስና ሰራዊት አባላት ስልጠና መስጠቱን ጠቁመው፤ከዚህ ውጭ ወደ ሶማሊያ የተሰማራ ሰራዊት እንዴሌለ አስረድተዋል፡፡

የኤርትራ መንግስት የተወሰኑ ታንኮችንና ወታደሮችን ወደ ፀጥታ ቀጠናው ማስገባቱን አቶ መለስ ጠቁመው፤ ከዚህ አኳያ አርትራ የአልጀርሱን ስምምነት በመጣሷ የፀጥታ ቀጠናው አለ ለማለት እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የኤርትራ መንግስት ወታደሮቹን ከፀጥታ ቀጠናው እንዲያስወጣ መግለጫ ቢያወጣም ታንክና ወታደር ያስገባሁት እህል ለመሰብሰብ ነው በማለት እንደቀለደበት የተናገሩት አቶ መለስ ኢትዮጵያ ጥቃቱን ለመከላከል ምንጊዜም ዝግጁ መሆኗን ግልጽ አድርገዋል

የኤርትራ መንግስት የሰላም ስምምነቱን ጥሶ ወንጀል በመፈጸሙ በመገፋፋት ኢትዮጵያ የምትወስደው አዲስ እርምጃ እንደሌለም አቶ መለስ አስገንዝበዋል፡፡

መንግስት ለሰላም ካለው ቁርጠኛ አቋም በመነሳት ከኤርትራ መንግስት ጋር ለመወያየት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም ያሉት የኤርትራ መንግስት ግን በጎ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ህገ መንግስቱን በሃይል ለማፍረስ ከመረጡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎችን በማሰባሰብ የኢትዮጵያን ህልውና ለማክሰም እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።

ከኦብነግ፣ ኦነግና ቅንጅት ጋር በተለያዩ ጊዜያት ድርድሮች ተካሂደው እንዳልተሳኩ ጠቅሰው፣አሁንም ከሻዕቢያ ጋር ሆነው ጦርነት በማወጃቸው ያሰቡትን ሊያሳኩ እንደማይችሉ በተግባር እንዲያረጋግጡ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም አስረድተዋል።

የመንግስት አቋም ህገ ወጥ እንቅስቃሴን በህጋዊ መንገድ ማክሰም፣ ህገ መንግስቱን ተቀብለው በሰላም ከሚታገሉ ጋር አብሮ መስራትና ድርድር ማካሄድ መሆኑን አስምረውበታል።

በኦሮሚያ ክልል ሰዎች ይታሰራሉ ተብሎ ለቀረበው ጥያቄም ወንጀል ከሰሩ መታሰራቸውና በህጋዊ መንገድ ለፍርድ መቅረባቸው አግባብ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ ውጭ የተከናወነ እስራተ ካለ መንግስት እያጣራ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ለምክር ቤቱ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ዓመታዊ የህግ ረቂቅ አወጣጥና መርሀ ግብር እንዲፀድቅ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በ318 ድጋፍ፣ በ3 ተቃውሞና በ112 ድምፅ ተአቅቦ መጽደቁን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።