አዲስ አበባን ለሚጎበኙ ቱሪስቶች ጠቃሚ መረጃ የሚሰጥ የአቅጣጫ ጠቋሚ ሶፍትዌር መስራቱን ብላክ ስታር የተባለ ድርጅት ገለጸ

አዲስ አበባ ጥቅምት 9/1999/ዋኢማ/ የውጭ ቱሪስቶች በአዲስ አበባ ከተማ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ያለማንም ዕርዳታ ወደ ፈለጉበት ቦታ መዘዋወር ሚያስችላቸው የአቅጣጫ ጠቋሚ ሶፍትዌር መስራቱን ብላክ ስታር የተባለ ድርጅት አስታወቀ። ሶፍትዌሩ የትራፊክ ፍሰትን ለመቆጣጠር የሚረዳ መረጃ እንደሚሰጥም ተመልክቷል።

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሩባቤል ክበበ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በ12 ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪካል፣ የሀርድና የሶፍትዌር ኢንጂነሮች የተሰራው "ቨርቹዋል አዲስ" የተባለው ሶፍትዌር የአዲስ አበባ ዋናዋና አካባቢዎችና የክፍለ ከተሞች ካርታን መሰረት በማድረግ ቱሪስቶች በጉብኝታቸው ወቅት የሚያስፈልጓቸውን ሙዚየሞች፣ ባንኮች፣ ሆስፒታሎችና ፖሊስ ጣቢያዎች አድራሻንና ሌሎች ጠቃሚ መረጃ የሚሰጥ ነው።

ሶፍትዌሩ በተገጠመለት የቱሪስት፣ የንግድና ኖርማል ሞድ ወይም የይዘት መለዋወጫ ቴክኖሎጂ በመታገዝም ከቱሪዝም በተጨማሪ የንግድ ሰዎችና ማንኛውም ነዋሪ የሚፈልገውን መረጃ ማግኘት በሚችል ሁኔታ የተዘጋጀ መሆኑንም አስረድተዋል።

በቱሪስት ሞዱ የሆቴሎች፣ ሙዚየሞች፣ የተለያዩ መስህብ ቦታዎች በምን ያህል ርቀትና የት እንደሚገኙ የሚገልጽ ሲሆን፤ በኖርማልና በቢዝነስ ሞዱ ደግሞ ባንኮች፣ የንግድ ማዕከላት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሆስፒታሎችና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎች የያዘ መሆኑን ተናግረዋል።

ሶፍትዌሩን በተሽከርካሪ ላይ በሚቀመጥ ላፕቶፕ አሊያም ለዚህ ተግባር በተዘጋጀና ተሽከርካሪ ላይ በሚገጠም ባለስክሪን ማሽን አማካይነት መጠቀም የሚቻል ሲሆን፤ አብዛኞቹ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች በቀላሉ ሊያገኙት በሚችል ደረጃ መዘጋጀቱን አቶ ዘሩባቤል ገልጸዋል።

ሶፍት ዌሩ የአገር ውስጥና ኢትዮጵያን በብዛት የሚጎበኙ የውጭ ቱሪስቶችን ግምት ውስጥ በማስግባት በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና ፈረንሣይኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፤ በመጪው ዓመት የሚከበረውን የሚሊኒየም ክብረ በዓል ለመከታተል ለሚመጡ ቱሪስቶች አገጋዥ እንደሚሆን አስረድተዋል።

ሚሊየኒየሙን ምክንያት በማድረግ የሚፈጠረውን የቱሪስቶች ፍሰት ሁኔታ በማጥናትም የሌሎች አገሮችን ቋንቋዎች ለመጨመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

ሶፍትዌሩ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ያለውን የትራፊክ ፍሰት ለመቆጣጠር የሚያስችል መረጃ እንዳለውና አንድ አሽከርካሪ በምን ያህል ፈጥነት በማሽከርከር ላይ እንደሆነ የሚገልጽ መረጃ እንደሚሰጥም አቶ ዘሩባቤል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሶፍትዌሩን ስትጠቀም ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ ያደረጋታል ያሉት አቶ ዘሩባቤል፤ ይሄም የኢትዮጵያን የአፍሪካ መዲናነት ይበልጥ እንደሚያጠናክርላት ተናግረዋል።

ሶፍትዌሩን አስመልክቶ የተጠየቁት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ማስፋፊያ መምሪያ ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ በቀለ ቱሪስቶች ከዚህ በፊት አዲስ አበባን ለመጎብኘት የወረቀት ካርታና መረጃዎች ብቻ ይጠቀሙ እንደነበር ገልጸው፤ ቴክኖሎጂው ችግሩን በማስቀረት በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

ቴክኖሎጂ ስራ ላይ ሲውል የቱሪስት ፍሰትን ያጠናክራል የሚል ግምት እንዳላቸው ገልጸው፤ በተለይ በመጪው ዓመት ለሚከበረው የሚሊኒየም በዓል ለማክበር ለሚመጡ ቱሪስቶች መልካመ አጋጣሚ እንደሆነ አስረድተዋል።

ሶፍትዌሩ በመጪው ወር ገበያ ላይ እንደሚቀርብም ታውቋል።